
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ሲያሠለጥናቸው የነበሩ 1ኛ ዙር ሚሊሻ ሠልጣኞችን አስመርቋል። የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ የወታደራዊና የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ከወረዳው የተለያዩ ቀበሌዎች ተውጣጥተው ለተከታታይ 15 ቀናት ሲከታተሉ የነበሩ ሠልጣኞች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ብርጋዴል ጄኔራል ጠቅለው ደምለው ተገኝተው ለሠልጣኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው የአካባቢያችሁን ሰላም ለማስጠበቅና የወረዳውን ልማት ለማስቀጠል በወታደራዊ፣ በአካል ብቃትና በአዕምሮ ዝግጁ እንድትሆኑ ሥልጠናውን መውሰዳችሁ ወሳን ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፀጥታ ቢሮ አማካሪ ኮለኔል ባምላኩ እንደገለፁት ሠልጣኞች ከሥልጠና ያገኙትን አቅም ተጠቅመው የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ሚሊሻ መምሪያ ኃላፊ ሰለሞን አልታዬ በበኩላቸው ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ወረዳው በጥሩ ሁኔታ አዲስና ነባር ሚሊሻዎችን በመመልመል የነበሩ አፍራሽ ውዥንብሮችን አልፎ ለዚህ ምርቃት በማብቃቱ በየደረጃው ለተሳተፉ አካላት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ሠልጣኞችም በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በሰጡት አስተያየት የተሰጣቸው የወታደራዊ፣ የአቅም ማጎልበቻ እና የአዕምሮ ዝግጁነት ብቃት ሥልጠና በጥሩ ሁኔታ በመከላከያ ታግዞ እንዲሰለጥኑ መደረጉን ገልፀው ከዚህ በፊት ከሰለጠኑ የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ሰላማቸውን ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከላይ የተገለፁ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኮረኔል ደረጀ ደበሳይ፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮማንደር ሰይድ ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተክለ ብርሃን አጥላባቸው፣ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ንጉሴ ሞገስ፣ ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኃላፊ ሜሮን አበበ፣ የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ደረሰ ደመመ እንዲሁም ሌሎች የወረዳው የፀጥታ መዋቅር እና ጽሕፈት ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል።
የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያመለክተው በሥልጠናው ጉልህ አስተዋፅዖና ተሳትፎ ለነበራቸው የዕውቅናና ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶ ምርቃት ተጠናቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!