በደብረ ብረሃን ከተማ አሥተዳደር አንደኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል ሊገነባ ነው።

37

ደብረብርሃን: ታኅሣሥ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ አምራቾችን እና ሸማቾችን በቀጥታ የሚያገናኝ 1ኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል ግንባታ ተጀመሯል። በግንባታ ማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም መሐመድ (ዶ.ር)፣ የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እና ሌሎች የክልልና የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የገበያ ማዕከሉ በ90 ሚሊዮን ብር ወጭ የሚገነባ ሲኾን የክልሉ ንግድና ገቢያ ልማት ቢሮ ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በጋራ የሚያሠሩት ይሆናል። ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀመርም ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ፣ ሕገ ወጥ ደላሎቾን ለመቆጣጠር፣ ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከልና የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳጠር ትልቅ ሚና ይኖረዋል። የገበያ ማረጋጋት ሥራዎችንም ያሳልጣል ተብሏል።

ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሚገነባው ማዕከሉ የሰብልና የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶች በየዓይነታቸው እንዲቀርቡበት ተደርጎ ዲዛይን ተዘጋጅቶለታል። ግንባታው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥም በልዩ ሁኔታ ክትትል ይደረግበታል ተብሏል።
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የማዕከሉ መገንባት በከተማዋ የተቀላጠፈ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊው ዶክተር ኢብራሒም በሰጡት ማብራሪያ ፕሮጀክቱ በልዩ ልዩ መመዘኛ መስፈርቶች ሰው ተኮር መሆኑን አስገንዝበዋል። የክልሉ መንግሥት ኅብረተሰቡን ከኑሮ ውድነት ለመታደግ የሚያስችሉ የገበያ ማዕከላትን በክልሉ በሚገኙ ከተማ አሥተዳደሮች ላይ ለመገንባት 800 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ጠቅሰዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብ እንዲሁም ሸማቹ ማኅበረሰብ ሕገ ወጥነትን በመከላከል የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። የገበያ ማዕከላት ግንባታ እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚጠናቀቅም ዶክተር ኢብራሒም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ምርታማነት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት እያስገኙ መሆኑን ገልጸዋል። አምራችና ሸማችን የሚያገናኝ ማዕከል መገንባቱ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል ትልቅ ድርሻ እንዳለውም አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም አሰከባሪና የሚሊሻ አባላት ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን በቁርጠኝነት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋገጡ።
Next articleበሰሜን ጎንደር ዞን ለሚሊሻ አባላት ወታደራዊ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።