
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ንቦች ከተለመደው የማር እና ሰም ምርት ባለፈ የዕጽዋትን ሽፋን በመጨመር፣ ጎርፍን በመቀነስ፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል እና የውኃ ሥርገትን በመጨመር ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ፋይዳቸው የጎላ ነው። የንብ ማነብ ሥራ የሰብል ምርትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ከፍተኛ ድርሻ አለው።
ንቦች ዕጽዋትን በማራከብ የሰብል ምርት ከ20 እስከ 140 በመቶ እንደሚያሳድጉ ጥናቶች ያሳያሉ። የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የንብ፣ ሐር ልማት እና ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ ሙሐመድ ጌታሁን እንዳሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚመረተው የምግብ ምርት አንድ ሦስተኛ የሚኾነው በንቦች የሚዳቀል ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰብልን በነፍሳቶች በማዳቀል በዓመት ከሚገኘው 200 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ውስጥ ደግሞ 15 ቢሊዮን ዶላሩ በንቦች በማዳቀል የሚገኝ ገቢ ነው። አሜሪካ 100 የሚኾኑ የሰብል አይነቶችን በንቦች በማዳቀል 15 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በዓመት ታገኛለች።
በእንግሊዝ አጠቃላይ በነፍሳት ከተዳቀለ ሰብል 690 ሚሊዮን ዩሮ በዓመት ይገኛል፡፡ ንቦች ሰብሎችን በማዳቀል ምን ያህል የምርት ጭማሪ እንደሚያስገኙ ለማሳየት የተወሰኑ የሰብል አይነቶችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። ኮረሪማ 35 በመቶ፣ ጥጥ 28 በመቶ፣ ተልባ 35 በመቶ፣ ወይን 29 በመቶ የምርት ጭማሪን ያስገኛሉ።
ጎመን ዘር 30 በመቶ፣ ሰላጣ 21 በመቶ፣ ጎመን 40 በመቶ፣ ብርቱካን 35 በመቶ እና እንጆሪ 112 በመቶ የምርት ጭማሪ ያስገኛሉ። ያልበሰለ ብርቱካን ከዛፉ አናት ላይ የመውደቅ አጋጣሚውን በ46 በመቶ እንዲቀንስ እንደሚያደርጉም ጥናቶችን ጠቅሰው ነግረውናል። እንደ እስራኤል ባሉ ሀገራት ደግሞ አናቢዎች ንቦችን ለሰብል አምራቾች ለድቀላ አገልግሎት ብቻ በማከራዬት በወር ለአንድ ቀፎ እስከ 80 ዶላር ገቢ እንደሚያገኙ ነው ባለሙያው የገለጹት።
በኢትዮጵያ ንቦች ሰብሎችን በማዳቀል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ የስንዴ ምርትን ከ50 እስከ 65 በመቶ፣ የሱፍ ምርትን ከ 21 እስከ 27 በመቶ፣ የኑግ ምርትን ከ33 እስከ 66 በመቶ፣ የአተር እና አፕል ምርትን ከ50 እስከ 60 በመቶ እንዲሁም ሀባብ እና ፓፓያን መቶ በመቶ ምርት የማሳደግ አቅም እንዳላቸው በ2010 ዓ.ም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያደረገውን ጥናት ጠቅሰው ነግረውናል።
የንቦች መኖር የማር ምርትን ከመስጠት ባለፈ ለሰብል ምርት ዕድገት የሚያመጣውን ፋይዳ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ልቅ በኾነ የጸረ አረም እና ጸረ ተባይ ኬሚካል ርጭት በኅብረ ንቦች ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በአማራ ክልል ልቅ በኾነ የጸረ አረም እና ጸረ ተባይ ኬሚካል ርጭት በዓመት ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደሚደርስ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጥናት ጠቅሰው ገልጸዋል።
ባለሙያው እንዳሉት በአማራ ክልል የንብ ማነብ ሥራ ከተለመደው የማር ምርት ባለፈ ለሰብል ምርታማነት አገልግሎት እንዲሰጡ እንደ ብር ሸለቆ እና አየሁ ጓጉሳ በመሳሰሉ ትልልቅ የእርሻ አካባቢዎች ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። በቀጣይም እንደ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ሁሉ ንቦችን እንደ አንድ ፓኬጅ ለመጠቀም በመንግሥትም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
አሠራሩ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው በመኾኑ እና አማካይ የምርት ጭማሪውም ከማዳበሪያ ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው በመኾኑ ይበልጥ ተመራጭ ያደርገዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!