
ጎንደር፡ ታኅሳስ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ፣ ታች አርማጭሆና ማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳዎች የሚገኙ ሚሊሻዎች ወደ ሥልጠና ማዕከላት ገብተዋል። ወደ ሥልጠና የገቡ ሚሊሻዎች በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሰዉን በደል እና ግፍ ለመከላከል፣ የአካባቢያቸውንም ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የተከሰተዉ የጸጥታ መደፍረስ በሕዝብ ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን እያደረሰ ይገኛል፡፡ በሥልጠና ማስጀመሪያው ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደሪ አወቀ አስፈሬ ችግሩን ለመቅረፍ ውይይቶች በተለያዩ ወቅቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል። ከውይይቶች በኋላ አንጻራዊ ሰላም በክልሉ ቢስተዋልም ችግሩ አሁንም እንዳልቆመ ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ ጥያቄ ሊፈታ የሚችለዉ በአፈሙዝ ሳይኾን በመነጋገር ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ወደ ሥልጠና ማዕከላት የሚገቡ ሰልጣኝ የሚሊሻ አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የሰላም እጦቱ የአርሶ አደሮችን ፣የነጋዴዎችን የተማሪዎችን ሕይዎት ፈተና ውስጥ ማስገባቱንም ተናግረዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ቤት ከመቀመጥ ሰላምን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾን እና መታገል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኝ የሚሊሻ አባላት የአካባቢዉን ሰላም በማስከበር አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
መንግሥት የሰላም አማራጮችን ቀደም ብሎ አቅርቧል ያሉት አሥተዳዳሪው አሁንም የሰላም አማራጮች ክፍት መኾናቸውን አስገንዝበዋል። በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ503ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል መዝገበ ዘሩ ለሥልጠና ወደ ማዕከላት የገቡ የሚሊሻ አባላት በክልሉ ያለውን የሰላም ችግር ለመቅረፍ ቁርጠኛ መኾን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ከሥልጠና በኋላ በየአካባቢያቸው ተሰማርተው አካባቢያቸውን ሰላም እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል። በመጀመሪያ ዙር ስልጠና ለመሳተፍ ወደ ማዕከላት የገቡ ሠልጣኝ የሚኒሻ አባላት በአካባቢያቸዉ ያለው የሰላም እጦት ሰላም ለማስከበር እንዳነሳሳቸዉ ተናግረዋል። ሠልጣኝ የሚኒሻ አባላት ወደ ሥልጠናው ሲገቡ በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መኾኑንም ገልጸዋል። ከሥልጠናዉ በሚያገኙትን ዕውቀትና ልምድ ተመርኩዘዉ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ሰላም ለማስከበር በሚደረገዉ ጥረት ሰላምን ለማስከበር ቁርጠኛ መኾናቸዉንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!