“ፍትሕ የሚጀምረው የእያንዳንዱን ግለሰብ መብት ስናከብር ነው” ፊቶል ሲያኮር

36

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀንን አክብሯል። በክብረ በዓሉ የሃይማኖት አባቶች፣ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች እና ተማሪዎች ተገኝተዋል። በዓሉ ስለ ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ እና ተማሪዎች ትምህርት የማግኘት መብት ውይይት ተካሂዷል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የሕግ ተማሪው ዮርዳኖስ ኃይሌ ሰብዓዊ መብቶች ማንኛውም ሰው ሰው በመኾኑ ብቻ የሚያገኛቸው መብቶች ናቸው ብሏል። የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል መብት እንዳለው ተናግሯል። ነገር ግን አሁን ላይ በርካታ ሰዎች ሰበዓዊ መብቶቻቸውን እየተነፈጉ ነው ብሏል።

በተለይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሰዎች ሰብዓዊ መብት እየተጣሰ መኾኑን ነው የተናገረው። የግለሰቦች እና የቡድኖች መብት መከበር እንዳለበትም ገልጿል። ሀገራት ሰላምን ከመስበክ ይልቅ ለጦርነት እሽቅድድም ላይ መኾናቸውንም አንስቷል። በግጭት ምክንያት ተማሪዎች የመማር መብታቸው መነፈጉንም አንስቷል።

የሰብዓዊ መብት ቀንን ማክበር የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም ገልጿል። ስለ ሰብዓዊ መብት ግንዛቤ መፍጠር እና እንዲከበሩ መሥራት ይገባል ነው ያለው። የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባልም ብሏል። ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባም ተናግሯል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የሕግ ተማሪዋ ላምሮት ጌታቸው በጸጥታ ችግሮች እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ሰብዓዊ መብቶች እየተገረሰሱ ነው ብላለች። የሰብዓዊ መብት ቀንን ማክበር መብቶች እንዳሉን ለማወቅ፣ የማይጣሱ እና የማይገረሰሱ መኾናቸውን ለማሳወቅ ያስችላል ነው ያለችው።

ለሰብዓዊ መብት መከበር ሁሉም ኀላፊነት እንዳለበትም ተናግራለች። ሕጻናት የመማር መብት እንዳላቸውም ገልፃለች። አሁን ያሉ ችግሮች ግን የሕጻናትን መብት እየነፈጉ ነው ብላለች። ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ተቋማትም መብቶች እንዲከበሩ መሥራት አለባቸው ነው ያለችው። በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት መብት እንዲከበር ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባቸዋል ብላለች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ቡድን መሪ ፊቶል ሲያኮር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ታኅሳስ 10/1948 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የሰብዓዊ መብት አከባበር ሰነድን ማጽደቁን አስታውሰዋል።

የሰብዓዊ መብት ሰነድ በጸደቀበት ቀንም ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ቀን ይከበራል። በተባበሩት መንግሥታት ደርጅት የጸደቀው የሰብዓዊ መብት ሰነድ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ዜግነት እና ሌሎች ልዩነቶች እና መድሎ ሳይኖር ሰዎች በእኩልነት መብታቸው እንዲከበር የሚደነግግ መኾኑን ነው የተናገሩት።

የሰብዓዊ መብት ቀንን ማክበር ለሰብዓዊ መብት መከበር የጋራ ኀላፊነቶቻችን እንድናስታውስ ያደርገናል ነው ያሉት። በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከድኅነት እና ከግጭት ጋር እየተጋፈጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

መንግሥታት፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከል እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ማንኛውም ሰው ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ የመኖር መብት እንዳለውም ገልጸዋል። ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም ሰው የክብር እና የነፃነት መሠረት መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ቀኑን ስናስብ ለሰብዓዊ መብቶች በየእለቱ ለመቆም፣ ደግ ለማድረግ እና ፍትሐዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት መኾኑ መቻል አለበት ነው ያሉት። ሰብዓዊ መብቶችን ለሁሉም እውን ለማድረግ ቃል መግባት መቻል አለብንም ብለዋል። የፍትሕ መጓደልን መዋጋት እና ለሰብዓዊ መብት መከበር መሥራት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

በጋራ ኾነን ሰዎች በእኩልነት እና በፍትሐዊነት የሚኖሩባትን ዓለም መገንባት እንችላለንም ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአርሶ አደሩ አምራች፤ የከተማ ነዋሪው ሸማች የኾነበት ልምድ በሌማት ትሩፋት መቀየር እንዳለበት ተገለጸ።
Next articleፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የጥራት መንደርን ጎበኙ።