
ደብረ ማርቆስ: ታኅሳሥ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳዳር ውስጥ የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ አባላት ሥልጠና ተጀምሯል። በመርሐ ግብሩ ለአዳዲስ እና ነባር ሰላም አስከባሪ አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚሰጥ የከተማ አሥተዳደሩ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ እሸቴ እስቲያውቅ ገልጸዋል።
ሰልጣኞች የሚሰጣቸውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመጠቀም የማኅበረሰቡን ሠላም ማስጠበቅ እንዲችሉ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። እስካሁን የከተማዋን እና የማኅበረሰቡን ሰላም ለማስከበር ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት መሠራቱንም አንስተዋል። ተወካይ ኀላፊው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሕገ ወጥ ተግባራትን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ይሄነው አበባው ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን ማኅበረሰቡ በሠላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ሰልጣኞች በአቅም፣ በዕውቀት እና በአመለካከት ብቁ ኾነው ማኅበረሰቡን ለማገልገል ቁርጠኛ መኾን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የከተማ አሥተዳሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ በውስጥ አቅማችን የከተማችንን ሰላም በማስከበር ኅብረተሰቡን የልማቱ ባለቤት ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል። ሠልጣኞች የተሰጣቸውን የሰላም ማስከበር ሥልጠና በመጠቀም የከተማዋንም ኾነ የማኅበረሰቡን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች እንደገለጹት የሚሰጣቸውን ሥልጠና በአግባቡ በመውሰድ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
