
አዲስ አበባ፡ ታኅሳስ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባንኩ ባለአክሲዮኖች 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው ላይ የተገኙት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ ጋሻው ደበበ አማራ ባንክ ባለፈው በጀት ዓመት በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ አዎንታዊ እና አሉታዊ ሁኔታዎች እንደነበሩ አንስተዋል።
አማራ ባንክ እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ ሥራ በጀመረበት ዓመት ከገጠመው ኪሳራ በመውጣት 550 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማስመዝገብ ችሏል ብለዋል። አማራ ባንክ እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር እስከ ሰኔ 30/2024 በድምሩ 25 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ በማሰባሰብ 20 ነጥብ 4 ቢሊዮን ለዋና ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዘርፎች እያቀረበ መኾኑ ተገልጿል።
ባንኩ የተደራሽነት አቅሙን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማሳደግ በሀገሪቱ ያለውን የቅርንጫፍ ብዛቱን ወደ 310 ከፍ አድርጓል። ባንኩ የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል። የባንኩ አጠቃላይ የሃብት መጠን ቀድሞ ከነበረበት በ24 በመቶ በመጨመር አሁን ላይ 35 ነጥብ 2 ቢሊዮ ብር መድረሱ ተመላክቷል።
የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል እና መጠባበቂያ ገንዘብም ከነበረበት 21 በመቶ እድገት በማስመዝገብ 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም በመድረኩ ተገልጿል::
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
