
አዲስ አበባ፡ ታኅሳስ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት (ኢደኢ) የብሔራዊ የጥራት ደረጃዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጧል። የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት (ኢደኢ) ከብሔራዊ የደረጃ ዝግጅት ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመኾን ብሔራዊ ደረጃዎችን በብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት ማፅደቁን አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ኅዳር 20 እና 26/2017 ዓ.ም ባካሄደው 40ኛ እና 41ኛ መደበኛ ስብሰባበ በስድስት ዘርፎች እና በ23 የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የቀረቡለትን 350 ደረጃዎች መርምሮ ማጽደቁን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ሃብቴ ገልጸዋል። የጥራት ደረጃዎች በስድስት ዘርፎች የተዘጋጁ ናቸው። ከቀረቡት 350 ደረጃዎች 207 ያህሉ አዲስ ናቸው። 143 ደረጃዎች የተከለሱ መኾናቸው ተገልጿል።
በግብርና እና በምግብ ዝግጅት 40፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል 79፣ በኬሚካል እና ኬሚካል ውጤቶች 68፣ በአካባቢ እና ጤና ደኅንነት 54፣ በጨርቃ ጨርቅ እና ቆዳ 15 እንዲሁም በግንባታ እና ሲቪል ምህንድስና 94 ደረጃዎች ናቸው ብለዋል ሥራ አስፈጻሚው። ከጸደቁት ደረጃዎች መካከልም 33ቱ አስገዳጅ ደረጃዎች ሲኾኑ የኤሌክትሪክ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ሲሚንቶ እና ጅብሰም፣ የብረት እና አልሙኒየም ስትራክቸሮች ተጠቃሽ ናቸው።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ.ር) በበኩላቸው እንደ ሀገር እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ ደረጃዎች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል። አሁን ላይ የፀደቁት ደረጃዎች ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ የጸደቁ ደረጃዎች ፦
👉የሰው እና እንስሳት ደህንነት ለማስጠበቅ
👉ለአካባቢ ጥበቃ
👉የምርቶችን ጥራት እና አገልግሎት ለማሻሻል እና ለማረጋገጥ
👉የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ
👉 የሸማቾችን ጥቅም ለማስጠበቅ
👉 በኢንዱስትሪ ዘርፉ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን እና የንግድ ተወዳዳሪነትን አቅም ለማጎልበት ወሳኝ ናቸው።
የግብርና ምርትን ወደ ውጭ በመላክ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷ እንዲያድግ እና ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥም ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለዋል። የጸደቁ ደረጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግም ድጋፍ እና ቁጥጥር ከሚያደርጉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ ሥለመኾኑም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
