
አዲስ አበባ: ታኅሳስ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክር ቤቱ ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰምቷል።
የምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ ክልሎች ተጀምረው ያልተጠናቀቁ እስከ 10 ዓመት የፈጁ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምን እየሠራ ነው ሲሉም ጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ.ር) ፕሮጀክቶቹ ግልጽ ባልኾነ መስፈርት በመመረጣቸው፣ በጥናት ያልተደገፉ በመኾቸው፣ የፕሮጀክት ዲዛይን ችግር በመኖሩ እና በበጀት እጥረት የተቋረጡ ናቸው ብለዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ችግር ለመፍታት ቋሚ መስፈርት ማዘጋጀቱን ጠቅሰው የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ እየተሠሩ ባሉ ሥራዎችም 21 ተቋርጠው የነበሩ ፕሮጀክቶች ማስተካከያ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓልም ነዉ ያሉት።

ከተጓተቱ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በአማራ ክልል የሚገኘው የርብ ፕሮጀክት መኾኑም በምክር ቤቱ ተጠቅሷል።
ይህ ፕሮጀክት የማጠቃለያ ሥራ የቀረው መኾኑን በመጥቀስ የጸጥታ ሁኔታው ሲፈቅድ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በዘንድሮ በጀት ዓመት አዲስ ፕሮጀክቶችን በማቆየት የተጓተቱን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ በጀት መያዙን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልሳ ጉኡሽ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
