
ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን በደተጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደረባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜን ሸዋ ዞን አንደኛው ነው፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ትውልድን በትምህርት የመታደግ ልዩ የንቅናቄ እቅድ ከወረዳ ትምህርት መሪዎች፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ጋር ምክክር አካሂዷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ፀጋየ እንግዳወርቅ የዞኑ የትምህርት ተሳትፎ አፈፃጸም በየዓመቱ እየቀነሰ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁናዊ የክልሉ የጸጥታ ችግር ለተሳትፎው መቀነስ በምክንያትነት የሚጠቀሱ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያመላክተው በዞኑ በ2017 የትምህርት ዘመን ተመዝግበው መማር ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከልም ከ318 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳልመጡም አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን የክልሉ ትምህርት በሰው ሠራሽና ተፈጥሮ ችግሮች ሲፈተን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ትውልዱን በመልካም ስነ ምግባር በማነፅ ረገድ ሚናው ትልቅ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ከ4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች እንዳልተመዘገቡ የተናገሩት ኃላፊው እነዚህን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት ሁለተኛ ዙር የተማሪ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		