በሙስና ሊጠፋ የነበረ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳኑን የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ።

30

ወልድያ: ኅዳር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙሰና ትግል የነገ ስብዕናን ይገነባል” በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ወሎ ዞን የፀረ ሙስና ቀን በፓናል ውይይት ተከብሯል።

ዞኑ ሙስናን እና ብልሹ አሠራሮችን በመታገል የመንግሥትን እና የሕዝብን ሃብት መታደጉን የሰሜን ወሎ ዞን ሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል የሥነ ምግባር መኮንን ደሳለኝ ማዕረጉ ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት በሙስና ክትትል እና ርምጃ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ነው የተናገሩት።

ላሊበላ፣ ሀራ፣ መርሳ፣ መቄት እና ሌሎች የወረዳ ከተሞች ላይ ያለአግባብ ተላልፎ የነበረን 74 ሺህ 300 ካሬ መሬት ማስመለስ ተችሏል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ 529 የሙስና ጥቆማ ደርሰው 312 አሥተዳደራዊ ርምጃ መውሰዱንም አስረድተዋል።

ለሕግ ከቀረቡት 114 ጉዳዮች ውስጥ 65 የሚሆኑት በመጣራት ላይ ናቸው ነው ያሉት።

ከሲቪል ሰርቪስ አኳያ ምልመላ፣ መረጣ እና ደረጃ ዕድገት ላይ ብልሹ አሠራር እንዳይኖር ክትትል እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እና ሌሎች ሰነዶች በአግባቡ አንዲፈተሹ የተቋማት ትብብር አስፈላጊ መኾኑም ተመላክቷል።

የመልካም አሥተዳደር እና የሕዝብ የቅሬታ ምንጭ የኾነውን ሙስናን በመፀየፍ እና በመታገል የሁሉም ሴክተር ሠራተኞች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ማርቆስ ከተማ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ግንባታ ተጀመረ፡፡
Next article“ጥራት ለሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ዋነኛ ተግባር ነው” ዶክተር መቅደስ ዳባ