
ጎንደር: 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
ተገልጋዮች በመንግሥት ተቋማት ጉዳያቸዉን ለማስፈፀም እንቅፋት ከሚፈጥሩባቸዉ ምክንያቶች ሙስና ተጠቃሽ ነዉ። ሙስና የተገልጋዮችን እርካታ እና የሀገር እድገትን ይገድባል።
የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስማማዉ ደሳለኝ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ሙስና እና ብልሹ አሠራር እየተበራከተ መጥቷል። ጽሕፈት ቤታቸዉ በዋነኛነት የግንዛቤ ፈጠራ እና ቅድመ መከላከል ሥራ ላይ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ተግባራት  22 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ከምዝበራ መታደግ ተችሏል ብለዋል። ብልሹ አሠራርን የመከላከል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት  ኀላፊው ኅብረተሰቡም እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም በሙስና ወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ በማሰር ላይ የተንጠለጠለ የፍትሕ አሠራር እንደነበር ያስታወሱት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ  አየልኝ ደሳለኝ አሁን ላይ ግን የተመዘበሩ ንብረቶችን ማስመለስ እንደሚያጠቃልል ተናግረዋል። እንደ መምሪያ ኀላፊዉ ገለፃ በተያዘዉ በጀት ዓመትም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ንብረት ተመልሷል። 
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን በተለያዩ ሁነቶች በጎንደር ከተማ አክብረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
        👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		