ግብር ከፋዮች ከየካቲት 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ብቻ የታተመ ደረሰኝ እንዲጠቀሙ ተወሰነ።

110

ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የገቢዎች ሚኒስቴር ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በደረሰኞች ላይ ልዩ መለያ ኮድ (QR – Code) አካቶ ማተም በሚያስችል አሠራር ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። ስምምነቱ የህትመት ጥያቄ መቀበል እንዲሁም ከታተመ በኋላ የስርጭት እና የቁጥጥር ሥርዓትን ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መሥራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የመግባቢያ ሰነዱን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽታሁን ዋለ ተፈራርመዋል። የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ሚኒስቴሩ እንደ ሀገር ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ገቢን በብቃት መሰብስብ እና ሀገራዊ ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት ማሳካት ነው ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህን ለማሳካት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለግብር ከፋዩ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ ማሻሻያዎችን አከናውኗል ብለዋል። ባለፉት ጊዜያት የማንዋል ደረሰኝ አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ ብዙ ርቀት ለመሄድ የተሞከረ ቢሆንም፤ የሀሰተኛ ደረሰኝ ህትመት መበራከት በግብር አሰባበሰቡ ላይ ፈተና ሆኖ መቆየቱንም አንስተዋል።

አያይዘውም ደረሰኝ እንዲታተም ፍቃድ ከመስጠት ጀምሮ ያሉ አገልግሎቶችን ማስተናገድ እንዲቻል የራሱ የሆነ ዲጂታል አሠራር የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀው፤ ደረሰኝ የሚያሳትም ማንኛውም ግብር ከፋይ በዚሁ መንገድ መስተናገድ የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል።

ከታህሳስ 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ ማንዋል ደረሰኝ የማሳተም ጥያቄ ማቅረብ የሚቻል መሆኑን አመላክተው፤ ከየካቲት 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ብቻ የታተም የማንዋል ደረሰኝ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በበኩላቸው ድርጅቱ ሚስጥራዊ ህትመቶችን በማተም ካለው የካበት ልምድ በመነሳት ደረጃውን የጠበቀ፣ ልዩ መለያ ኮድ (unique QR code) የተካተተበት እና አስመስሎ መሥራት የማይቻል የህትመት ሥራ ለማከናወን በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

አክለውም፥ ግብር ከፋዮች ለገቢዎች ሚኒስቴር በሚያቀርቡት የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ መሠረት የሚቀርቡ የህትምት ትዕዛዞችን ተቀብሎ ደረሰኞችን ለማተም ቅድመ ዝግጅት ስለመደረጉም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ሕግ የማስከበር ሥራዉ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
Next articleበአዲስ አበባ ለልማት ተነሺዎች በሁሉም ክፍለ ከተሞች 8 ሺህ ቤቶች ተገነቡ።