
ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ ዕድል ተጠቅመው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡ የኢትዮ ቼክ ሪፐብሊክ የጋራ ቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያን ጁሬስካ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ውጤት ማስመዝገባቸውን በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሡሩም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በኢትዮጵያ የተካሄደው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትኾን ማድረጉን ገልጸዋል። በቅርቡ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡ የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎችም በተፈጠረው ምቹ አጋጣሙ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ልምድ እና አቅም ያላት ቼክ ሪፐብሊክ በዘርፉ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ትብብር እንደምታጠናክር ተገልጿል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች መዳረሻ ከሆኑ የአውሮፓ ሀገራት መካከል አንዷ ቼክ ሪፐብሊክ ናት ። በቀጣይም የኢትዮጵያ ምርቶች የበለጠ እንዲገቡ ለማድረግ እንደሚሠራ አምባሳደር ብርቱካን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!