
ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከኅዳር 16/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የነጭ ሪቫን ጸረ ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ የማጠቃለያ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሄዷል። መድረኩን የአማራ ሴቶች ማኅበር ከተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።
በመድረኩ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም፣ የአማራ ሴቶች ማኅበር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ እጅጋየሁ መኮንን፣ የአማራ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር ገነት ወንድሙ እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ሀገራችን ከሚፈለገው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንድትደርስ እና ከድህነት ተላቅቃ የዜጎች መብት እኩል የሚከበርባት እንድትኾን የሴቶች ተሳትፎ የላቀ ነው ብለዋል። የሴቶች መብት እና ጥቅሞቻቸው ሊጠበቁ እና ሳይሸራረፉ ሊተገበሩ ይገባል ነው ያሉት። ይህንን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ነው ያመላከቱት፡፡
አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መኖራቸውንም አመላክተዋል። በማንኛውም መልኩ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሴቶች ለሀገር ልማት የሚደያደርጉትን የልማት አስተዋጽኦ የሚገድብ ነው ብለዋል። እንደ የዩኒሴፍ መረጃ በዓለም ላይ 370 ሚሊዮን ሴቶች የጾታዊ ጥቃት ሰለባ ናቸው ያሉት ኃላፊው 79 ሚሊዮን የሚኾኑት ደግሞ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ናቸው ነው ያሉት። የጸጥታ ችግር፣ ለወንጀሎች የሚወሰዱ እርምጃዎች አስተማሪ አለመኾን እና ጉዳዩን አስመልክቶ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎች ጥብቅ አለመኾናቸው ጥቃቶች በአይነትም፣ በመጠንም፣ በጉዳትም ከፍ እንዲሉ አስችሏል ብለዋል፡፡
የሴቶችን ጥቃት የማስቆም ሥራ የወንዶችን አጋርነት በእጅጉ ይፈልጋል ነው ያሉት። የነጭ ሪቫን ቀን ዋና ዓላማም ወንዶች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሴቶችን ጥቃት እንዲከላከሉ ለማስቻል መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የአማራ ሴቶች ማኅበር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ እጅጋየሁ መኮንን ማኅበሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለሴቶች ሁለንተናዊ ለውጥ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች እንዲቀንሱ እና እንዲቆሙ በትኩረት የሚሠራ ማኅበር መኾኑን አንስተዋል። ሴቶች በርካታ እና ውስብስብ ችግሮች እየገጠሟቸው ነው ያሉት ምክትል ቦርድ ሰብሳቢዋ በተለይም በግጭት እና ጦርነት አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች ለጥቃት እየተጋለጡ ቆይተዋል ብለዋል። ጥቃቶችን የማስቆም ሥራ ለተወሰነ ተቋም ብቻ የሚተው አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ መኾኑን በመረዳት በጋራ ቆሞ መሥራት ግድ እንደሚል አስገንዝበዋል። የአማራ ሴቶች ማኅበር ዳይሬክተር ገነት ወንድሙ ማኅበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለ26 ዓመታት ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይም ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ አስተዋጽኦ ያደረገ ተቋም ነው ብለዋል።
“የሴቷ ጥቃት የእኔም ጥቃት ነው፣ ዝም አልልም” በሚል መልዕክት ከኅዳር 16 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድየቆየው ንቅናቄ ሴቶች ለመብታቸው እንዲቆሙ፣ የሚደርሱ ጥቃቶች የሚወገዱበት እና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትም ለማረጋገጥ ያለመ ነበር ብለዋል። ንቅናቄው ለተወሰኑ ቀናት መካሄዱን ያነሱት ዳይሬክተሯ የሚስተዋለውን የተዛባ የሥርዓተ ጾታ ግንዛቤ በማስተካከል የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የማሳደግ ሥራ ግን ቀጣይነት ያለው ነው ብለዋል፡፡ ሥራው የምንግዜም ተግባር ኾኖ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
ማኅበሩ የሴቶችን ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ የሥርዓተ ጾታ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሚያከናውንም ገልጸዋል። ቀድሞ ከመከላከል በተጨማሪ ጉዳቱ የደረሰባቸው ሴቶች ሲያጋጥሙም የሥነ ልቦና፣ የጤና እና የኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲያገኙ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም የሴቶች ጥቃት እንዲያበቃ ሁሉም በማንኛውም ጊዜ ትግል ማድረግ እንደሚገባው አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!