የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሀገር ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡

65

ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሰማሩ ባለሃብቶች የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እና ተኪ ምርት በማምረት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መኾኑን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ አስታውቋል፡፡
የቅርንጫፉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥሩዬ ቁሜ በፓርኩ በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የተሠማሩ ባለሃብቶች መሠማራታቸውን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማስፋት፣ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት፣ ለአርሶ አደሮች ምርት የገበያ ትስስር በማመቻቸት እና የሥራ እድል በመፍጠር ለኢኮኖሚው እድገት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ በትራንስፎርመር ማምረት እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማሩ አምስት ባለሃብቶች በሥራ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ሥራ አስኪያጇ ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ እና ተኪ ምርት የሚያመርቱ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

” ኒርቫና” ፋብሪካ የዘይት ድፍድፍ እና የተከካ አኩሪ አተር በማምረት ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ እና ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግብዓት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው በመጀመሪያው ዙር የተከካ አኩሪ አተር ምርት ወደ ውጭ በመላክ 304 ሺህ ዶላር ገቢ ማስገኘቱን አመልክተዋል። 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው ተኪ ምርት በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

ሁለተኛ ዙር የምርት ውጤት ወደ ውጭ ለመላክ በዝግጅት ላይ እንዳለም ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው ከ9 ሺህ 500 የአኩሪ አተር አምራች አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ራሱን የቻለ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ፣ የተደራጀ ዳታ ቤዝ እና ደኅንነቱን የሚያስጠብቅ “ሲሲ ቲቪ” ካሜራ የተገጠመለት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ እንደ ኢዜአ ዘገባ ፓርኩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት የተገነባለት፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት መኾኑን ገልጸዋል።

በፓርኩ ሦስት ሼዶች እና 96 ሄክታር መሬት ያልተያዘ እንዳለ የተናገሩት ሥራ አስኪያጇ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ፓርኩ በመምጣት ወደ ልማት እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኒርቫና ፕሮሰሲንግ ፋብሪካ የመጋዘን ማናጀር ቢንያም ዓለማየሁ ፋብሪካው ሥራ በጀመረ በአራት ወራት ውስጥ በቀን 600 ኩንታል የተከካ አኩሪ አተር እና 10 ቶን ድፍድፍ ዘይት በማምረት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት እየሠራ ነው ብለዋል።

በ150 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው እና በውስጡ ስምንት ሼዶችን የያዘው የባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ካደጉ ፓርኮች አንዱ መኾኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሰሞኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢጋድ የህጻናት ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
Next articleየሴቶች መብት እና ጥቅሞቻቸው ሊጠበቁ እና ሳይሸራረፉ ሊተገበሩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አሳሰበ።