
ባሕር ዳር: ኅዳር 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የህጻናት ጉዳይ ሚኒስትሮች የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍን ለማጽደቅ በመጪው አርብ በአዲስ አበባ ይሰበሰባሉ። ስብሰባው የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍን በማፅደቅ በዓባል ሀገራት እና በቀጣናው ያሉ ህጻናት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ያለመ መኾኑን ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ይህ ደግሞ አባል ሀገራቱ ለህፃናት መብት መከበር ከገቡት ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ቃል ኪዳኖች ጋር የሚጣጣም ነው ሲል ኢጋድ በመግለጫው ጠቅሷል። ሚኒስትሮቹ የኢጋድ የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍን በማጽደቅ ወደ ሥራ እንዲገባ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሚኒስትሮች ስብሰባ ከታኅሳስ 4 እስከ 6 ቀን 20217 ዓ.ም የሚካሄድ ሲኾን ከሚኒስትሮቹ ስብስባ አስቀድሞ ታኅሳስ 2 እና 3 ቀን 2017 ዓ.ም የቴክኒክ ባለሙያዎች ስብስባ እንደሚካሄድ ታውቋል።
በስብስባው ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና የልማት አጋሮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መግለጫው አመልክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!