
ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ቀደም ሲል የተጀመሩ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታን አጠናቅቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው አስታውቀዋል። መሰረተ ልማት ባልተዳረሰባቸው ሰፈሮች የአዳዲስ መንገድ ግንባታ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ተመልክቷል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንደገለጹት፤ ቀደም ባሉት ዓመታት ተጀምረው አፈጻጸማቸው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ፕሮጀክትን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። በተያዘው ሳምንት ውስጥ የ7 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የማጠናቀቂያ አስፋልት የማልበስ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የማጠናቀቂያ ግንባታ እየተካሄደባቸው ያሉት ከፋሲሎ -ጉዶ ባሕር፣ ከሆራይዘን – አዴት መስመር እና ከባለእግዚአብሔር – ሳብስቴሽን የሚገኙት ናቸው ብለዋል። በተጨማሪም ከአየር መንገድ በማርዳ ቀለም ወደ መብራት ኀይል ሳብስቴሽን በሚወስደው መንገድ ላይ እስከ 3 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የአስፋልት ማልበስ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ከአየር መንገድ በማርዳ ቀለም-ወደ መብራት ኀይል የሚወስደው 8 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ውጭ ያሉት ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል። ያደሩ ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት የማጠናቀቂያና የአዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች የማብሰሪያ ምእራፍ ነው ያሉት አቶ ጎሹ፤ ከተማዋን ለማልማት ቁርጠኛ አቋም ተወስዶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም መሰረተ ልማት ባልተዳረሰባቸው ሰፈሮች አዳዲስ የአስፋልት፣ የድንጋይ ንጣፍና የጠጠር መንገድ ግንባታ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም አመልክተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በከተማዋ የመሰረተ ልማት ግንባታን አጠናክሮ በማስቀጠል ኅብረተሰቡን በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!