“ሁሌም ስለሰላም አስፈላጊነት በመነጋገር ልማታችንን እናስቀጥል” የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ

89

ደሴ: ኅዳር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በወቅታዊ የሰላምና ልማት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡ በመድረኩ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኀላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም፣ የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ፣ የደሴ ከተማ ነጋዴዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ “ሰላምና ልማት ሊነጣጠሉ አይችሉም ፣ ሰላም ከሌለ ልማት አይኖርም፣ ልማት ከሌለ ሰላም አይኖርም፤ ሁሌም ስለሰላም አስፈላጊነት መነጋገር ይገባናል” ብለዋል፡፡ ኢኮኖሚው ላይ በትኩረት መሥራት ለፖለቲካዊ መረጋጋት አስፈላጊ ስለመሆኑም ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተናገሩት፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ከኅብረተሰቡ እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰላምን ማስፈን በመቻሉ የልማት ሥራዎች እንደተከናወኑ የተናገሩት ከንቲባው ባለፈው በጀት ዓመት 14 የተለያዩ ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም የኮሪደር ልማትና ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የሰላምን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሐጂ መሐመድ ከበደ እና አቶ መሐመድ ጌቶ ነጋዴው ማኅበረሰብ ነግዶ የሚያተርፈው፣ ግብር የሚከፈለው እና የልማት ጥያቄ የሚኖረው በመጀመሪያ ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል፡፡

ለደሴ ከተማ ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱ የገለጹት የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ብልሹ አሠራር ያላቸው፣ ለተገልጋዩ በቅንነት እና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ የማይሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች በመኖራቸው ከተማ አሥተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስተካክል ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ:- ከድር አሊ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ940 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ጠቅላላ ትርፍ አገኘ።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ የ7 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር አስፋልት የማልበስ ሥራ በመፋጠን ላይ ነው።