
አዲስ አበባ: ኅዳር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር የባለአክሲዮኖች 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባዔ በአዲስ አበባ አካሂዷል። በጉባዔው የ2016 በጀት ዓመት ባንኩ ያከናወናቸው ጠቅላላ ተግባራት ቀርበዋል።
የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዓለም አስፋው
አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ለሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት ከአገልግሎት ውጭ ኾነው የቆዩ ቅርንጫፎች ወደ ሥራ መመለሳቸውንም ገልጸዋል። በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ተጨማሪ አዳዲስ ቅርንጫፎችን መክፈታቸውንም አንስተዋል።
ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከ940 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ጠቅላላ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቀዋል። የተገኘው ትርፍ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ26 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የገለጹት። የሒሳብ አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር እሰካሁን ከ2 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም ተናግረዋል። የባንኩ አጠቃላይ ሃብት 43 ቢሊዮን ብር ደርሷል ነው ያሉት።
አጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 35 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት ሊቀመንበሩ ከባለፈው ዓመት ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱን አንስተዋል።
ባንኩ ስመጥር ከኾኑ ከአሥር በላይ ዓለማቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ትሥሥር ፈጥሮ ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ይህም ለደንበኞች አማራጮችን ከማስፋት ባለፈ ቀጣይ ለሚኖረው የውጭ ምንዛሬ ግኝት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።
ባንኩ ቀጣይነት ያለው ትርፋማነትን ለማረጋገጥ፣ ደንበኞች ካሉበት ኾነው በፈለጉት ስዓትና ሁኔታ የባንኩን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባንኩ በቀጣይ ዘመኑን የዋጁ እና የደንበኞችን ፍላጎት ያማከሉ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመሥጠት ትኩረት ሠጥቶ ይሠራልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!