
ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሚዲያ ለሀገራዊ አንድነት እና ለብሔራዊ ጥቅም” በሚል መሪ ሃሳብ ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መሪዎች እና ሠራተኞች በባሕርዳር ከተማ እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት፣ በጣና ዳር እየተገነባ የሚገኘው ጣና ማሪ እና የባሕር ዳር ስታዲየም ደግሞ የጎበኟቸው ልማቶች ናቸው።
በከተማዋ እየተገነቡ የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች የሚያስደስቱ መኾናቸውን ገልጸዋል። ከዘገባ ሥራ ባለፈ የልማት ሥራዎችን መጎብኘት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር እንደሚያደርግም ተናግረዋል። በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጉምዝኛ ቋንቋ አርታኢ ጉርሜሳ መንገሻ በከተማዋ ባያቸው ሥራዎች መደሰቱን ገልጿል። ለከተማዋ ውበትን የሚያልብሱ፣ ለነዋሪዎቿ የተመቹ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን መመልከቱን ነው የተናገረው። እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲጨምር እንደሚያደርግም ገልጿል።
ለአብነት የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በስፖርቱ ዘርፍ ኢትዮጵያውያንን ከዚያም ሲያልፍ አፍሪካውያንን የሚያገናኝ፣ መግባባት እና አንድነት የሚፈጠርበት፣ ከተማዋን የሚያሳውቅ ነው ብሏል። ያደረጓቸው ጉብኝቶች ዘገባዎችን ተረድቶ ለመሥራት እንደሚያግዝም ተናግሯል። የልማት ሥራዎች ማኅበራዊ ትስስር እንዲፈጠር እና ኢኮኖሚ እንዲያድግ እንደሚያደርጉም አመላክቷል።
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የኽምጣና ቋንቋ ዘጋቢ ገብረኪሮስ ታረቀ የጎበኛቸው የልማት ሥራዎች የክልሉንና የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት አቅም የሚያሳድጉ ናቸው ብሏል። በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአማራ ራዲዮ ዘጋቢ ስማገኝ አብርሃም በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ለከተማዋ ገቢ ማምጣት የሚችሉ መኾናቸውን ተናግራለች። የማኅበረሰብን ሕይወት እንደሚቀይሩና ለሀገር እድገትም የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብላለች።
የከተማዋን ውበት የሚገልጡ መኾናቸውንም ተናግራለች። ጋዜጠኞች የልማት ሥራዎችን ሲጎበኙ ታዓማኒ የኾኑ ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚያስችላቸውም አመላክታለች። በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የምልክት ቋንቋ ዜና አቅራቢ ፍቅርተ ዘገየ በጎበኟቸው የልማት ሥራዎች አዲስ ጉዳዮችን ማየታቸውን ተናግራለች። ጋዜጠኞች የልማት ሥራዎችን በተግባር ሲመለከቱ እውነት ላይ የተመሠረተ ዘገባዎችን ለመሥራት እና የልማት ሥራዎችን ለመከታተል ያስችላል ነው ያለችው።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መሠረት አስማረ ጉብኝቱ ሚዲያ ለሀገራዊ አንድነት እና ለብሔራዊ ጥቅም ያለውን አስተዋጽኦ በገቢር ለማሳየት ያለመ ነው ብለዋል። ንድፈ ሃሳብን ከተግባር ጋር አጣምሮ ማየት የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠር ያስችላል ነው ያሉት።
የተደረገው ጉብኝት በተግባር ያለውን ሥራ ለማየት እና ከዚህ ባሻገር ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ያግዛል ብለዋል። ጋዜጠኞች ንድፈ ሃሳብን እና ተግባርን እያቆራኙ ሲሄዱ ሀገራዊ አንድነትን እና የጋራ የኾነ ትርክትን ለመገንባት ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
ጋዜጠኛ ዘርፈ ብዙ ዕይታ እንዳለው የተናገሩት ዳይሬክተሩ ጋዜጠኞች የተለያዩ ሥራዎችን ሲመለከቱ የጋራ የኾኑ ጉዳዮችን እንዲያጎሉ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ጋዜጠኞች የልማት ሥራዎችን ሲመለከቱ የተሻሉ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡና ተጨማሪ ሃሳቦችን እንዲያመነጩ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሃሳቦች እንደተቀየሩ፣ የማድረግ አቅምም እያደገ፣ የይቻላል መንፈስ እየጎለበተ መኾኑን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል። የጋዜጠኞችን የዕይታ አድማስ የሚያሰፋ እና የተሻለ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያነሳሱ ናቸው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!