
ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን በግዳን ወረዳ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ፅንፈኛ ቡድን በተደጋጋሚ የወረዳዋን ዋና ከተማ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በገባበት ወቅት በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል። ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ 2 ላንድ ክሩዘር መኪናዎችን አቃጥሏል።
ራሱን “ፋኖ ” እያለ የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን ለከተማው ፅዳትና ውበት ሥራ አገልግሎት የምትሰጥ 1 ዳማስ መኪና አቃጥሏል፤ ሕዝብ አገልግሎት እየሠጠ ከሚገኘው አማራ ባንክ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ዘርፏል፤ ለእናቶች እና ህፃናት አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበረ 1 አንቡላንስን ከሆስፒታል ሲመለስ መንገድ ላይ በማገት ወስዷል።
ፅንፈኛው በእጅጉ ክፋት የተሞላበት እና የሕዝብን ሃብትና ንብረት ማውደም እንዲሁም ዝርፊያ የመፈፀም ድርጊቱን ሁሉም አካል በሚገባ ተረድቶ ቡድኑን እንዲያወግዝ መገለጹን ከአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!