
ደሴ: ኅዳር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ሰርኬ ሽፈራሁ እና መሬማ ሙሔ በኮምቦልቻ ከተማ ቢራሮ ክፍለ ከተማ የራስ አገዝ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው። ልጆቻቸውን ያለአባት በችግር ሲያሳድጉ ዓመታትን ገፍተዋል።
በዚህ ጥረት ላይ የመኖሪያ ቤት ችግር ከባድ መኾኑን የገለጹ ሲኾን በተለይም በክረምት ወቅት አስቸጋሪ ጊዜን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል። ይህ ችግር ተቀርፎ በማየታቸው ደስተኛ መኾናቸውን የገለጹት እናቶች አሁን ላይ የመኖሪያ ቤት በማግኘታቸውም ምስጋና አቅርበዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቢራሮ ክፍለ ከተማ ራስ አገዝ ቀበሌ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች የተገነባ ቤት ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ “ብልጽግና ፓርቲ ትኩረት ከሰጣቸው ሰው ተኮር ተግባራት መካከል ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ማድረግ ነው” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት 44 ቤቶች እየተሠሩ መኾኑን የገለጹት ከንቲባው ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተሠርተው የተጠናቀቁ ሰባት ቤቶችን ለነዋሪዎች ማስረከብ መቻሉን ተናግረዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ ለሌሎች አካባቢዎች ትምህርት እንደሚኾን የገለጹት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) “ለአቅመ ደካማ ወገኖች የተሻለ ኑሮ ለመፍጠር በጋራ መሥራት ይገባዋል” ብለዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የኮምቦልቻ ከተማን በተለያየ አግባብ የመደገፍ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ሕይዎት አስማማው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!