ጻታዊ ጥቃን በመከላከል ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አሳሰበ።

49

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መምሪያው 33ኛውን ዓለም አቀፍ የነጭ ሪቫን ቀን በፓናል ውይይትት አክብሯል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ፈንታነሽ አፈወርቅ በዓሉ “የሴቷ ጥቃት የእኔም ነው፤ ዝም አልልም” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው ብለዋል።

የበዓሉ መከበር በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጻታዊ ጥቃት በመከላከል በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ንቅናቄን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል። ኀላፊዋ እናቱን፣ እህቱን፣ ሚስቱን እና ልጁን እንዲሁም ሀገሩን የሚወድ ሁሉ በሴት ላይ ጥቃት አያደርስም ነው ያሉት። በዚህ የሰላም እጦት ወቅት ደግሞ ከምንጊዜውም በላይ ሴቶች የተጎዱበት በመኾኑ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እና ጻታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆም በቁርጠኝነት የምንነሳበት ወቅት ሊኾን ይገባል ብለዋል።

ሴቶችም ጥበበኛ ልባቸውን ተጠቅመው በየአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ወደ ሰላም እንዲመጡ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ኀላፊዋ አሳስበዋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ላቀች ሰማ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመከላከል ሁሉም ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት። ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በአብዛኛው ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በቅርብ ሰዎች የሚፈጸም ነው ያሉት ወይዘሮ ላቀች ጥቃት ሲደርስም ለፍትሕ አካላት ጥቆማ በመስጠት በነጻነት የሚኖሩበትን ዓለም መፍጠር ለነገ የማይባል ተግባር መኾኑንም አስገንዝበዋል።

የውይቱ ተሳታፊዎችም ከወቅታዊ የፀጥታ ችግሩ ጋር በተያያዘ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። ችግሩን ለመሻገርም የሁሉንም አካላት ቅንጅት የሚጠይቅ በመኾኑ በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት።

በመድረኩ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሥራ ኀላፊዎች፣ ግብረሰናይ ደርጅቶች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልል ርእሰ መሥተዳድሮች አርባምንጭ ከተማ ገቡ።
Next articleየጽንፈኛው ታጣቂ ቡድን ከፍተኛ አመራሮች ምህረት ጠይቀው ገቡ።