8ኛው ኦዳ አዋርድ ተካሄደ።

26

አዲስ አበባ: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2010 ዓ.ም የተለያዩ የኦሮሞኛ ቋንቋ ሙዚቀኞችን እና አርቲስቶችን በመሸለም የተጀመረው ኦዳ አዋርድ ለ8ኛ ጊዜ ሽልማቱን አከናውኗል። በዘንድሮው ሽልማቱም ከሀገር አልፎ የአፍሪካ ሀገራት አርቲስቶችን አካትቶ ሽልሟል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ ኪነ ጥበብ ሕዝብን በማስተሳሰር ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በጋዜጠኛ በሻቱ ቶለማርያም የተጀመረው ኦዳ አዋርድ በበሻቱ መልቲሚዲያ እና በሌሎች አጋር አካላት የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሰዎችን ሲሸልም ቆይቶ 8ኛውን ሽልማት ከኢፌዴሪ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመኾን የ2017 መድረኩን አካሂዷል። በዚህ ዓመትም ለ2ኛ ጊዜ ከኢትዮጵያ አልፎ የምሥራቅ አፍሪካ አርቲስቶችን አካቶ ሸልሟል ሲሉ የገለጹት አዘጋጇ ጋዜጠኛ በሻቱ ቶሎማርያም ኦዳ አዋርድ ጥሩ የሠሩትን እያበረታታ የአፍሪካውያን እየኾነ ይገኛል ብለዋል።

ዩጋንዳዊውን ኤዲ ኬንዞ እና የኤርትራዋ ሚለንን ጨምሮ ከስምንት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት 18 አርቲስቶች በሽልማቱ ተካትተዋል። የዓመቱ ምርጥ የግጥም መጽሐፍ እና የምርጥ መጽሐፍ ሽልማቶች የተሰጡ ሲኾን በ2016 ዓ.ም ተስፋ የተጣለባት ድምጻዊት አሳንቲ አስቹ ተሸላሚ ኾናለች።

የዓመቱ ምርጥ ሴት ድምጻዊት ለምለም ኃይለ ሚካኤል ዋሊኒ በተሰኘው ሙዚቃ አሸናፊ መኾን ችላለች።

የ2016 ዓ.ም ምርጥ የዘመናዊ ሙዚቃ አሸናፊ ሲቦይ አጃም ኾኗል።

የ2016 ዓ.ም ምርጥ የጥንድ ሙዚቃ አደም መሐመድ እና ጫልቱ ቡልቶ አሸንፈዋል።

የ2016 ዓ.ም የሕይዎት ዘመን ተሸላሚ የጉራጊኛ ድምጻዊ ደምሴ ተካ ኾኗል።

ሌላኛው በሕይዎት ዘመን ተሸላሚ ደግሞ ክቡር ዶክተር ኪሮስ ዓለማየሁ የተሸለሙ ሲኾን ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ሽልማቱን ተቀብለዋል።

ምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ አርቲስት ሽልማትን ድምጻዊት ሚለን አሸንፋለች።

የዩጋንዳው ኤዲ ኬንዞ፣ የሩዋንዳው ብሩሲ ሜሎዲ፣ የደቡብ ሱዳን እና ሌሎች አርቲስቶችም በልዩ ልዩ ዘርፎች አሸንፈዋል።

በሽልማት መርሐ ግብሩ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮሪደር ልማቱ የተነሱ የኮንቲነር ባለይዞታዎችን መልሶ ለማቋቋም እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleየአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልል ርእሰ መሥተዳድሮች አርባምንጭ ከተማ ገቡ።