በኮሪደር ልማቱ የተነሱ የኮንቲነር ባለይዞታዎችን መልሶ ለማቋቋም እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

30

ጎንደር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘውን ጨምሮ የከተማው ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት በኮሪደር ልማት የተነሱ ሕጋዊ የኮንቲነር ባለይዞታዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚገነባውን የገበያ ማዕከል ሸድ አስጀምረዋል። በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በርካታ የኮንቲነር ባለይዞታዎች ለሕዝቡ አገልግሎት በመስጠት እራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ሲያሥተዳድሩ ቆይተዋል።

የሚጠበቀውን ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ሽግግር እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ በኮሪደር ልማት ተነሽ የኾኑ ሕጋዊ የኮንቲነር ባለይዞታዎችን መልሶ ለማቋቋም በሦስት ክፍለ ከተማዎች ለገበያ በተጠኑ እና ምቹ በኾኑ አራት ሳይቶች ላይ በ358 ሚሊዮን ብር ወጭ የገበያ ማዕከል ሸድ ግንባታ ዛሬ ተጀምሯል።

የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የልማት ተነሽዎችን መልሶ ለማቋቋም በአራት ሳይት የገበያ ማዕከል በፍጥነት ግንባታውን በማጠናቀቅ ለልማት ተነሽዎች ርክክብ ይካሄዳል ብለዋል።

በአዘዞ ክፍለ ከተማ በሁለት ሳይት፣ በማራኪ ክፍለ ከተማ እና በፋሲል ክፍለ ከተማ አንድ ሳይት የገበያ ማዕከላት ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ እየተገነቡ ነው። ሥራውን ሌት ተቀን በመገንባትም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል በኮሪደር ልማት የተነሱ ሕጋዊ የኮንቲነር ባለይዞታዎችን መልሶ በማቋቋም ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ አልመው እየሠሩ መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

በከተማዋ ያሉትን ሁሉንም ኮንቲነሮች በማንሳት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ከተማዋን የሚመጥኑ የገበያ ማዕከል መገንባት ላይ ካቢኔያቸው አልሞ እየሠራ መኾኑን ከከተማ አስተዳደሩ ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተሳሳተ መንገድ የጽንፈኛ ቡድኑ አባል ኾነው ሕዝባቸውን ሲበድሉ የቆዩ ከ300 በላይ ታጣቂዎች በይቅርታ ተመለሱ።
Next article8ኛው ኦዳ አዋርድ ተካሄደ።