“የፀና ሀገር ለመገንባት የጋራ ትርክት ያስፈልገናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

9

ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን “ሚዲያ ለሀገራዊ አንድነት እና ለብሔራዊ ጥቅም’ በሚል መሪ ሃሳብ ለሠራተኞቹ ስልጠና እየሠጠ ይገኛል። በሥልጠናው ማሥጀመሪያ መርኃ ግብርም የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተው ሥለ ሥልጠናው ዓላማ መልእክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ይርጋ ሲሳይ በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ በፍጥነት ከስኬት ላይ ስኬት እያስመዘገበ፣ የሀገራችን ስብራቶች እየጠገነ ተሻጋሪ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ብለዋል። ዴሞክራሲን ለማጽናት እና ለመትከል ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ይርጋ የሀገረ መንግሥት፣ የብሔረ መንግሥት እና የተቋም ግንባታ ሥራዎችን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ለዘመናት ታስቦ እና ተሠልቶ በተሠራው የተዛባ ትርክት ምክንያት የብሔርተኝነት እና የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ የሰላም መናጋት ሲያደርሱ መቆየታቸውንም ገልጸዋል። ሕዝብን ለማደናገር እና ለአፍራሽ ተልዕኮ የተጠቀሙበት ደግሞ ሚዲያን ነው ብለዋል። አሚኮ እጅግ ውስብስብ፣ ተለዋዋጭ እና አስቸጋሪ በኾኑ ዓመታት ጫናዎችን ተቋቁሞ፣ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ፣ ሕዝብን በማገልገል እውነተኛ የሕዝብ ተቋም መኾኑን አረጋግጧል ነው ያሉት። አሚኮ የድኅረ እውነት ዘመቻዎችን መቋቋም የቻለ ነውም ብለዋል።

አሚኮ እስካሁን የተወጣቸውን ኃላፊነቶች ይበልጥ ለማጠናከር እና ለማሳደግ ስልጠናው አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል። ስልጠናው ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ለመገንባት፣ የጋራ የኾነ እና ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያሰባስብ ገዥ ትርክት እንዲኖር የሚያስችል የሚዲያ ሥራ ለመሥራት አቅም እንደሚኾን አስገንዝበዋል።

ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ስልጠናው በሙያችሁ ሕዝባችሁን ለማገልገል የምታደርጉትን ጥረት የበለጠ ውጤታማ እንዲኾን የሚያስችል ነው ብለዋል። ስልጠናው የሀገርን የወደፊት እድገት እና እጣ ፋንታ፣ የሕዝብን የጋራ ፍላጎት በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እድል ይሰጣል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ “የፀና ሀገር ለመገንባት የጋራ ትርክት ያስፈልገናል” ነው ያሉት።

ሥልጠናው የሀገር እና የሕዝብን ፍላጎት ለማሳከት ምን ዓይነት ትርክት እንደምንከተል ግልጽ ግንዛቤ የሚፈጠርበት መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ወቅት ያጋጠመን ችግር የተዛባ ትርክት ውጤት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የተዛባ ትርክት ለአስከፊ የጸጥታ ችግር እንዳጋለጠም አንስተዋል። የእያንዳንዳችን እውነት ቢኖረንም የጋራ የኾነ እውነትም አለን ብለዋል።

ከጋራ ትርክቶች ይልቅ ለተናጠል ትርክቶች ቅድሚያ በመስጠታችን ችግር ሲገጥመን እንደቆየም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም ስልጠናው ሀገሪቱ የምትከተለውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና አተገባበር ግልጽነት የሚፈጥር መኾኑንም አብራርተዋል። የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመገንዘብ ሕዝብ እና መንግሥትን ድልድይ ኾኖ ለማገናኘት ያስችላል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በንጹሐን ላይ የጅምላ ፍጅትን በመፈፀም የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ የለም” የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር
Next articleበተሳሳተ መንገድ የጽንፈኛ ቡድኑ አባል ኾነው ሕዝባቸውን ሲበድሉ የቆዩ ከ300 በላይ ታጣቂዎች በይቅርታ ተመለሱ።