“በንጹሐን ላይ የጅምላ ፍጅትን በመፈፀም የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ የለም” የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር

9

ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር በደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማ በንጹሐን ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም ጽንፈኞች በንጹሐን ላይ ያደረሱት የጅምላ ግዲያ የገዳዮችን የጭካኔ ጥግ ያሳየ ድርጊት ነው ብሏል።

በደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማ የጽንፈኛ ቡድኑ ከ90 በላይ የሚኾኑ ንጹሐንን ከመስከረም 29/2017 ዓ.ም ጀምሮ በግዞት ካቆየ በኋላ ከእያንዳንዳቸው እስከ አንድ ሚሊየን ብር ካልከፈላችሁ እገላችኋለሁ እያለ ቤተሰብንም ጭምር በማንገራገር ገንዘቡን መቀበሉን አንስቷል። ገንዘቡን ከወሰደም በኋላም ኅዳር 26/2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 6:00 ሰዓት ላይ በሀገር መከላከያ ሠራዊቱ የደረሰበትን ምት መቋቋም ሲያቅተው ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ 37 ንጹሐንን በጅምላ ጨፍጭፏል ነው ያለው።

መጠሪያውን የማይቀበለው ግን ደግሞ በምግባሩ ጽንፈኛ እና አሸባሪ የኾነው ቡድን ለአማራ ሕዝብ የቆመ መስሎ የአማራን ሕዝብ አደናገሪ እንጅ በተግባር ሲታይ በሕዝብ ላይ የተጣበቀ ጸረ አማራ መዥገር ነው ብሏል በመግለጫው። በአማራ ሕዝብ የታሪክ ሂደት ውስጥ የዚህ ዓይነት ድርጊትን ያደረሰ የውስጥም ኾነ የውጭ ጠላት ኖሮ አያውቅም ነው ያለው።

ጽንፈኛው ቡድን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ አስመልሳለሁ በሚል ካባ ሕዝቡን እያሰቃየ መኾኑንም አመላክቷል፡፡ ልጆቹን ከትምህርት ገበታ አግዷል፣ ትራንስፖርት አስተጓጉሏል፣ ለእናቶች መድኃኒት እንዳይቀርብ አድርጓል፤ ሌሎች እኩይ ተግባራትንም ፈጽሟል ብሏል በመግለጫው። ጽንፈኝነት ለአብሮነት ጸር ከመኾኑም በላይ ራስን በራስ የማጥፊያ መሣሪያም ነው የምንለው በንድፈ ሃሳብ ሳይኾን በተግባርም እንደታየው ከራሱ ተናጠላዊ እውነት ውጭ የሚቆሙትን በሙሉ ስለሚበላ ነው ብሏል።

ችግሩ በዚህ ልክ ከኾነ ደግሞ ድርጊቱን በአርምሞ ከመመልከት ይልቅ በግልፅ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ የዚህ ዓይነት ኢ-ሰዋዊ ድርጊት ለማኅበረሰብ መስተጋብራዊ ሂደት ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ የከፋ ስለሚኾን የዞኑ ሕዝብ በቃህ ሊለው እንደሚገባም አመላክቷል።

መላው የፈረስ ቤት ከተማ ማኅበረሰብ በሙሉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችን በጅምላ ከወደቁበት አንስታችሁ በሀገራዊ ባሕል አልቅሳችሁ የቀብር ሥርዓታቸውን ስለ ፈፀማችሁ ምስጋናችንን እናቀርባለን ነው ያለው በመግለጫው።

ለተጎጅ ወዳጅ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል። የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ከወረዳው አሥተዳድር ጋር በመኾን አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መኾኑንም ገልጿል።

የዞኑ አስተዳደር በንጹሐን ላይ የጅምላ ፍጅትን በመፈፀም የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ የለም ብሏል በመግለጫው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከቤተሰብ ጋር በመደራደር ወንጀለኞችን ለማስለቀቅ መሞከር መቆም ይገባዋል” የሴቶች ማኅበር
Next article“የፀና ሀገር ለመገንባት የጋራ ትርክት ያስፈልገናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ