“ከቤተሰብ ጋር በመደራደር ወንጀለኞችን ለማስለቀቅ መሞከር መቆም ይገባዋል” የሴቶች ማኅበር

17

ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጉዳዩ የተከሰተው ኮምቦልቻ ላይ ነው። አንዲት ሩጣ ያልጠገበች ወጣት በቅርብ ቤተሰቧ ጥቃት ይደርስባታል፡፡ ጥቃቱ ለሕግ እንዳይደርስ ወንጀለኛው የማስፈራራት ሥራ እየሠራ ቢቆይም በመጨረሻ እንደምንም ጉዳዩን ለጓደኛዋ ታስረዳለች፡፡ ይህን የሰማችው ጓደኛዋ ስትፈራ ስትቸር ለወላጆቿ ትናገራለች። ጉዳዩን የሰሙ ወላጆችም ለሚመለከተው አካል ጉዳዩን እንዲያጣራ መረጃ ይሰጣሉ፡፡

መረጃው የደረሰው የሕግ አካልም ጉዳዩን ይዞ አስፈላጊውን የሕግ ቅጣት ለማስቀጣት ጥረት ቢያደርግም ሌላ ያላሰበው ክስተት ይገጥመዋል፡፡ የልጅቷ ቤተሰቦች በውስጥ ተደራድረው ጉዳዩን በመጨረስ ሸፋፍነው ለማስቀረት በሚል ተነጋግረው ተስማሙም፡፡ ክሱ ማስረጃ እንዳይኖረው በማድረግም ጉዳዩ ተዳፍኖ ወንጀለኛው ቅጣት እንዳያገኝ ኾኖ እንዲቀርም ሰፊ ርብርብ አደረጉ። ይህም ማስረጃ ያጣው የሴቷ በደል ተዳፍኖ እስካሁን አለ ሲል ነበር የአማራ ሴቶች ማኅበር ለአሚኮ የገለጸው፡፡

የሴቶች ጥቃት ከጊዜ ጊዜ በዓይነትም በመጠንም እየጨመረ እንደሄደ የሚናገሩት የአማራ ሴቶች ማኅበር ምክትል ዳይሬክተር ሁሉአየሽ አወቀ ይህን ጥቃት ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ወሳኝ እንደኾነ በመገንዘብ እየሠሩ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡ በተለይም በፕሮጀክት ወንዶችን ጨምሮ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ያካተተ የማኅበረሰብ ውይይት በጉዳዩ ላይ እንደሚካሄድ ነው ያስረዱት፡፡

በመደበኛውም ቢኾን ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው ከጥቃቱ በመለስ ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ሁለንተናዊ ችግሮች ለማሳወቅ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ጥቃት ከደረሰም በኋላ ቢኾን ችግሩን ለማስገንዘብ የገንዘብ እጥረት ያለባቸውን መደገፍ የሥነ ልቦና እና ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጤና እክሎች ስለሚኖሩ እንዲታከሙ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት፡፡

በተለይም ጥቃት አድራሹ ለሌላው ማኅበረሰብ የሚያስተምር ቅጣት እዲያገኝ ከሚመለከታቸው የሕግ አከላት ጋር በመኾን እየሠሩ እንደሚገኙም ነው ያስገነዘቡት፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር አኳያ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ሴቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ከማስተማር ባለፈ ችግሮች ሲከሰቱ በአፋጣኝ የሕግ አካላትን ማግኘት እንዲችሉ እና ማኅበረሰቡም ስለ ጥቃቱ መረጃ የሚሰጥበትን ሁኔታ እየፈጠሩ ስለመኾናቸውም አስረድተዋል፡፡

የነጻ የስልክ መስመር በመዘርጋት ጥቃቶች ሲኖሩ መረጃ የሚደርስበትን ሁኔታ እየፈጠሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የችግሩ ባለቤት ኾኖ ጥቃት አድራሹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ አለመተባበር፣ ምስክር አለመኾን፣ መደራደር፣ በቤተሰብ በመደራደር ወንጀለኞችን የማስመለጥ ሁኔታ በመኖሩ ኀብረተሰቡ ቆም ብሎ እንዲያስብ እና ጥቃቶችን በጋራ መከላከል እንዲቻል አሳስበዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ሴቷ ጥቃት ሲደርስባት የወደፊት ኅልሟ እና የምታስበው ሁሉ እንደሚበላሽባት፣ በራሷ መተማመን እንዳትችል፣ ፈሪ እንድትኾን እና በራሷ ቁማ እችላለሁ በሚል ሥራ እንዳትሠራ የሚያደርግ የሥነ ልቦና ችግር እንደሚገጥማት በመገንዘብ ሁሉም ቆም ብሎ በማሰብ ከሴቶች ጎን እንዲሰለፍ ጠይቀዋል፡፡

መደፈሩ አሁን ላይ ከፍ እያለ በቤተሰብም ጭምር እየተከሰተ ነው የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሯ ኮምቦልቻ ላይ፣ ደብረ ማርቆስ ላይ፣ ባሕር ዳር እና መሰል ቦታዎች ላይ በተጨማጭ ችግሩ መጥቶ ጉዳዩን እየተከታተሉ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው የነጭ ሪቫን ቀንም እየጨመረ የመጣውን የሴቶች ጥቃት ለመከላከል ታሳቢ አድርገው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሠሩ ስለመኾኑም ነው የነገሩን፡፡

የአማራ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ማሪቱ ፈንታሁን እንደነገሩን የነጭ ሪቫን ቀን ከሕዳር 16/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 16 ቀናት በሴቶች ጥቃት መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቷ የሴቶችን ጥቃት መከላከል የሚቻለው የወንዶችን አጋርነት ማግኘት ሲቻል እንደኾነ ገልጸው ይህን ለማድረግም ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለመኾኑ አብራርተዋል፡፡

ከሴቶች ጥቃት አኳያ አሁን ላይ አለመማራቸው፣ ከትምህርት ገበታ መገለላቸው፣ በቤተሰብ እና በሚያውቋቸው ጭምር እየተጠቁ በመኾኑ ይህ ድርጊት እንዲወገዝ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ባሉ አደረጃጀቶች ክልሉ ላይ ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር ታሳቢ ተደርጎ የተለያየ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

ሴቶች ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ የሚደርስባቸው የሥነ ልቦና ችግር ቀርቦ ለማስረዳት ስለሚቸገሩ አስተማሪ የኾነ ቅጣት ለማስቀጣት እንዳልተቻለም ነው ያብራሩት፡፡ በደረሰባቸው ጥቃት ከሚደርሰው የመገለል ሁኔታ በተጨማሪ ራሳቸውን እንዲያጠፉም ምክንያት እየኾነ በመኾኑ ሁሉም በጉዳዩ ላይ በትብብር እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡

ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ወደ ሕግ አቅርቦ ለማስቀጣት በተደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ ምስክር እና ጠበቃ በመኾን ስለማይተባበር የደረሱ ወንጀሎች ሕግ ፊት ቀርበው ማስረጃ በመታጣቱ ፋይሉ እንዲዘጋ የሚኾንበት እና ወንጀለኞች በነጻ የሚሰናበቱበት ሁኔታ እየገጠመ ነው ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ይህን ተገንዝቦ ፍትሕ እንዲረጋገጥ እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ 43 የታጠቁ አካላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ተመለሱ።
Next article“በንጹሐን ላይ የጅምላ ፍጅትን በመፈፀም የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ የለም” የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር