
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጫና የሚበዛባቸው፣ ኀላፊነት የሚደራረብባቸው ሴቶች ሕመም ለምን አያመንም? የቤት መሰሶዎች፣ የትዳር መሠረቶች፣ የሀገር አለኝታዎች ሴቶችን ከጥቃት መጠበቅ ስለ ምን አልተቻለም? ግጭቶች በተበራከቱ፣ ፈተናዎች በበዙ፣ ውጣውረዶች ባየሉ ቁጥር በሥነ ልቦና የሚጎዱት፣ በአካል የሚሰበሩት፣ የሚደሙት፣ የሚቆስሉት ብዙዎች ናቸው። ጥይት በተተኮሰ ጊዜ ወዮ ልጄ እያሉ የሚደነግጡት፣ ምን ይመጣብን ይኾን እያሉ የሚጨነቁት፣ በሥነ ልቦና የሚጎዱትም አያሌ ናቸው።
ታዲያ ሕመማቸውን የሚሰማቸው፣ ጭንቀታቸውን የሚጨነቅላቸው፣ ብሶታቸውን የሚባስላቸው፣ አይዟችሁ ብሎ የሚያበረታቸው እምብዛም ነው። ይልቅስ ጫና የሚያበዛባቸው፣ መከራ የሚያጠነክርባቸው፣ የሥነ ልቦና ጉዳት የሚደራርብባቸው ብዙ ነው። የአማራ ሴቶች ማኅበር ከተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ በሚተገበረው የፕሮጀክት አስተባባሪ እና የሥነ ልቦና አማካሪ ደሌ ካሳው ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በሥነ ልቦና ጫና ተጠቂዎች ናቸው፣ በተለይም ደግሞ በሴቶች ላይ የከፋ ነው ይላሉ። ለምን ከተባለ? ባሎቻቸው፣ ልጆቻቸው እና ወንድሞቻቸው በጦርነት ውስጥ ይሳተፋሉ፣ በዚህም ምን ይፈጠር ይኾን የሚለው ለሥነ ልቡና ጫና ይዳርጋቸዋል።
ይህ ብቻ አይደለም ግጭት ሲከሰት በቀላሉ መሸሽ አይችሉም። ተፈጥሯዊ ጫናውም የበለጠ ለሥነ ልቦና ጫና ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ነው የሚሉት። ወንዶች ግጭት ሲፈጠር ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል በፍጥነት ከጥቃት ቀጣና ይወጣሉ። ሴቶችን ግን በፍጥነት የመውጣት እድላቸው ጠባብ ነው ይላሉ።
ሴቶች ለጾታዊ ጥቃት የተጋለጡ በመኾናቸው የሥነ ልቦና ስብራት ይገጥማቸዋል፣ የትኛውም ጥቃት የሥነ ልቦና ጉዳትን ይዞ ይመጣል ነው የሚሉት።
ጻጣታዊ ጥቃት የሚደርስባት ሴት የሥነ ልቦና ጥቃትና ስብራትም አብሮ ይደርሳባታል ይላሉ። በግጭት ወቅት የሚከሰት የሃብት እና ንብረት መውደም ከፍተኛ የኾነ ሥነ ልቦናዊ ጫና ያሳድርባቸዋል ነው ያሉት። የሴቶችን አካላዊ እና የሥነ ልቦና ጥቃት ለመከላከል ከሴቶች ላይ ብቻ ሳይኾን ወንዶች ላይም መሥራት ይገባል ነው የሚሉት። ሴቶችን ለከፋ የሥነ ልቦና ጫና የሚዳርጋቸው የሰላም እጦት ነው የሚሉት አማካሪው ሰላምን ማዝለቅ የሴቶችን ጥቃት ይቀንሳል፣ የሥነ ልቦና ጫናውንም ያስቀራል ይላሉ። እንደ አማካሪው ገለጻ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የወንዶች ሚናም ከፍ ያለ ነው።
የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ሴቶች ላይ ብቻ መሥራት አይገባም፣ ወንዶች ላይም መሥራት ያስፈልጋል፣ ብዙ ወንዶች ስለ ሴቶች ጥቃት ግንዛቤውም የላቸውም ይላሉ። እናቱ፣ እህቱ እና ሚስቱ እንዲደፈሩበት አይደለም እንዲነኩበት የሚፈልግ ወንድ የለም፤ ነገር ግን በሌሎች ላይ ጥቃት ያደርሳል። ይሄ ትልቅ የግንዛቤ ችግር ነው።
በእነርሱ ቤተሰቦች እንዲደርስ የማይፈልጉትን ነገር በሌሎች እንዳያደርሱ ወንዶችን ማሳተፍ እና ግንዛቤ ላይ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። አንዳንዴ የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርጋ የምታውቅን ሴት መድፈር እንደመድፈር የማይቆጥሩ ወንዶች አሉ፣ ይህ ስህተት ነው፣ መድፈር የሚያመጣውን የሥነ ልቦና ጫና አይረዱትም ነው የሚሉት።
ሴቶች የግንዛቤ ፈጠራ በሚያገኙባቸው ጉዳዮች መሳተፍ አለባቸው፣ በርካታ ሴቶች ጥቃት ቢደርስባቸው እንኳ ምን ማድረግ አንዳለባቸው አያውቁም፣ ይሄን ለማስተካከል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ያስፈልጋቸዋል ይላሉ። በሴቶች ላይ የሚደርሰው የሥነ ልቦና ጉዳት በማኅበረሰብ እና በሀገር ላይም ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ነው የሚሉት። የሥነ ልቦና ጉዳት ከሌሎች ጉዳቶች ሁሉ የተለየ ነው የሚሉት አማካሪው የሰው ልጅ አካሉ ቢጎዳ ተክቶ የሚሠራባቸው አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ሥነ ልቦናው ከተጎዳ ግን ሁሉም ነገር የተጎዳ ይኾናል ይላሉ።
የአንድን ሰው ሥነ ልቦና መጉዳት ማለት የአንድን ዛፍ ስር እንደመቁረጥ ይቆጠራል ነው ያሉት። በሥነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች በፍጥነት በሥነ ልቦና ባለሙያዎች መደገፍ ካልተቻለ የከፋ ጉዳት ይዞ ይመጣል ይላሉ። በሥነ ልቦና የተጎዱ ሴቶች ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ያገልላሉ፣ ማኅበረሰቡም ያገላቸዋል። በአንድ ወንድ ጥቃት የደረሰባት ሴት ሌሎች ወንዶችንም መጥላት፣ ከወንዶች ሁሉ መራቅ ታመጣለች። ይህ ደግሞ በቶሎ ካልተገራ እየከፋ እና እየሰፋ ይሄዳል ነው የሚሉት።
ሴቶች የአንዲት ሀገር ግማሽ አካሎች ናቸው፣ ያለ ሴቶች ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ማምጣት አይቻልም፣ ስለዚህ ሴቶችን ከጥቃት መጠበቅ ሀገርንና ማኅበረሰብን መጠበቅ ነው ይላሉ።
በአማራ ክልል ተደጋጋሚ የኾነ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ ድርቅና ሌሎች ችግሮች መኖራቸውን የተናገሩት አማካሪው ይህ ደግሞ ሴቶችን ለጥቃት እና ለሥነ ልቦና ስብራት ያጋልጣል። ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ብቻ ሳይኾን መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማትም መሥራት አለባቸው ይላሉ። መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በአማራ ክልል ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
የፍትሕ ተቋማት የንቃተ ሕግ ላይ ሥልጠና መስጠት እንደሚጠበቅም አንስተዋል። ሴቶች በምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ አለመኾን ለጥቃት እንዲጋለጡ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል። ሴቶች ሃብት እንዲያፈሩ፣ በፖለቲካ እና በማኀበራዊ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ ማድረግ ጥቃቱን ይቀንሰዋል።
ሚዲያዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
