
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሥርዓተ ጻታ ሴት ወይም ወንድ ከሚለው ከተፈጥሯዊ መገለጫ የዘለለ ትርጓሜ አለው። ሰው ሲወለድ ሴት ወይም ወንድ ነው፤ ከውልደት በኋላ ግን ሴትነት እና ወንድነት አረዳዱ ለየቅል ነው። የሥርዓተ ፆታ ምሁራን እንደሚሉት ከውልደት በኋላ ያለው አረዳድ ነው ሥርዓተ ፆታ የሚባለው። በጥቅል አረዳዱን ስንመለከት ወንዶች ጠንካራ፣ ሴቶች ደካማ፤ ወንዶች ጎበዝ እና በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ሴቶች ፈሪ እና በራሳቸው የማይተማመኑ የሚሉ ብያኔዎች ተሠጥተዋል።
እነዚህ የተዛቡ ብያኔዎች ሴቶችን ከትውልድ ትውልድ፣ ከዘመን ዘመን የተሻገረ በደል እዲደርስባቸው አድርጓል ይላሉ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ፆታ ምሁሩ አማኑ መኮንን። በማኅበረሰባችን ብዙ ወላጆች ሴት ልጅ ተምራ ትልቅ ደረጃ ትደርስልኛለች ብለው ከማስተማር ይልቅ ለትዳር ነው የሚያዘጋጇት፤ በሌላው መልኩ በሀገራችን ሴትን ልጅ ጠልፎ የሚወስድ ወንድ እንደ ጀግና የሚቆጥር ማኅበረሰብ አለ ነው የሚሉት ምሁሩ።
አሁን ላይ እየተለመደ የመጣው ፆታዊ ጥቃት የተዛባውን አስተሳሰብ እንደ በጎ ነገር የተለማመደ ትውልድ በመፈጠሩ ነው ብለዋል። ምሁሩ የሚያነሱት ሌላው ምሳሌ በዘመናዊው ዓለም ሴት ልጅ ዳኛ ኾና ብይን ትሠጣለች። በአንፃሩ ደግሞ በባሕላዊው ሽምግልና ሴት ልጅ ለሽምግልና ስትመረጥ ዓይታችሁ ታውቃለችሁ ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ። ሴትን ለሽምግልና እንዳትመረጥ ያደረጋት የተጣላን ማስታረቅ ስለማትችል ሳይኾን ማኅበረሰባችን ለሴቶች የሰጠው የተዛባ ብያኔ ውጤት ነው ይላሉ።
የሥርዓተ ፆታ ምሁሩ እንደሚሉት ግማሽ ያህሉ የሕዝብ ቁጥሯ ሴት ለኾነባት ኢትዮጵያ “ሴት ወደ ማጀት፣ ወንድ ወደ ችሎት” የሚለው አስተሳሰብ እስካልተቀረፈ ድረስ የእድገቷ ማነቆ ኾኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። በሀገሪቱ የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት እየሠራ ያለውን ሥራ በበጎ የጠቀሱት ምሁሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሴቶች የመሬት ባለቤት አልነበሩም፣ መንግሥት በሠራው ሥራ ሴቶች የመሬት ባለቤት መኾን ጀምረዋል ብለዋል።
ነገር ግን ይሄን ለአብነት እነሱ እንጂ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ሴቶች ተጠቃሚ አይደሉም የሚል እምነት አላቸው። ሴቶች እኩል ከወንዶች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ካስፈለገ በማኅበረሰባችን ውስጥ ሰፊ ቦታ የያዘው የወንድ የበላይነት አስተሳሰብ በልኩ መኾን አለበት ይላሉ።
የሴቶች እኩልነት የሚረጋገጠው ደግሞ መንግሥት ለሥርዓተ ፆታ ልዩ ትኩረት በመስጠት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች በተከታታይ ማስተማር ሲቻል ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!