
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ላይ እየጨመረ የመጣውን የሴቶች ጥቃት ለመከላከል ሁሉም ትኩረት እንዲሰጥ ታሳቢ ያደረገ የነጩ ሪቫን ቀን በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች እየተከበረ ነው፡፡ ይህ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ለ16 ቀን የሚቆይ ቢኾንም ተግባሩ ግን ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅ ነው፡፡
በአማራ ክልል ሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ምጥን ብርሃኑ የሴቷ ጥቃት የኔም ጥቃት ነው በሚል መሪ መልዕክት የግንዛቤ ፈጠራ ንቅናቄው ሲካሄድ ወንዶች በዋናነት አጋር እንዲኾኑ ይፈለጋል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ንቅናቄ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የተቋቋሙ ማኅበራት በሰፊው የሚሠሩበትን ሁኔታ መፍጠር የንቅናቄው ዋና ትኩረት እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ በንቅናቄ ብቻ ለውጥ እንዲመጣ ሳይኾን ዓመቱን በሙሉ እንዲሠራ ለማስታወስ ታስቦ እንደሚካሄድም ነው የነገሩን፡፡ በሥርዓተ ጾታ እኩልነት ውስጥ ዋናው ችግር የግንዛቤ ማነስ መኾኑን ነው ያስረዱት፡፡ የሕዝብ ግንኑነት ኀላፊዋ ጥቃት ሲባል በተለያየ ዘርፍ ተክፍሎ እንደሚታይም አስታውሰዋል፡፡
ጥቃት አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ጾታዊ እና ኢኮኖሚ ጥቃት ሊኾን እንደሚችል የተናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ በእነዚህ ጥቃቶች ላይ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ግንዛቤ ኑሮት ሴቷ ጥቃት እንዳይደርስባት ርብርብ እንዲያደርግ ታሳቢ ያደረገ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ ችግሩ ሳይፈጠር ቀድሞ መከላከል ላይም በትኩረት እንደሚሠሩ ነው ያስረዱት፡፡
ችግሩ ከደረሰም በኋላ ሴቶች የሥነ ልቦና ጉዳት እንደሚያጋጥማቸው የተናገሩት ኀላፊዋ ችግር ለመፍታት የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመስጠት ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራም እንደሚሠራ ነው ያብራሩት፡፡ ጥቃት የደረሰባት ሴት ልዩ እንክብካቤ ስለምትፈልግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላቱን በቁሳቁስ እና አስፈላጊ በኾኑ ነገሮች የማጠናከር ሥራም እንደሚሠራ ነው የገለጹት፡፡
በተለይ ጥቃት ደርሶባቸው የነገው ሕይዎታቸው ጨለማ መስሎ ለሚታያቸው ሴቶች ቀጣዩ ጊዜ ብሩህ እንደኾነ ለማሳየት የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚጠይቅም ነው ያስገነዘቡት፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ ከሴቶች በተጨማሪ የወንዶች እገዛ እና ከጎናቸው መቆም እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት። ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ሕይዎታቸውን ለመለወጥ በቋሚ የገቢ ማስገኛ እንዲሰማሩ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በቋሚ የገቢ ማስገኛ እንዲሰማሩ እየሠራ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡በረቀቀ ስልት በዚህ ዘመን እየተፈጸመ ያለውን የሴቶች ጥቃት ግንዛቤ በመፍጠር መከላከል ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ነው የገለጹት። በዓለም አቀፍም ኾነ በሀገር አቀፍ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የወጡ የሕግ ማዕቀፎች ተግባራዊ እንዲኾኑ ቢሮው ተፈጻሚነታቸውን እንደሚከታተል አስገንዝበዋል፡፡
የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ጥቃት ደርሶባቸው ለመጡ ሴቶችም ኾኑ ሕጻናት ሁሉአቀፍ አገልግሎት የሚሰጡ በክልሉ 17 ያክል የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋፋት ሥራ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!