የሴቶችን ጥቃት በዘላቂነት ለመፍታት ቅንጅታዊ አሠራርን እንደሚጠይቅ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።

14

ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክቶሬት የሴቶች እና ሕጻናት ክፍል አስተባባሪ ወንድወሰን ይፍሩ በሴቶች ላይ የሚፈጠሩ ጥቃቶችን ምላሽ ለመስጠት ኀላፊነት አለብን ብለዋል። ለጾታዊ ጥቃቶች ምላሽ ከመስጠት አኳያ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ የትኛውንም ወንጀል ምርመራ የማድረግ፣ ወንጀልን መርምሮ ክስ የማቅረብ እና ተከራክሮ የማስወሰን ኀላፊነት እንዳለበትም አብራርተዋል።

ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ነጻ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኙ እና ጉዳታቸው እንዲካስ ይደረጋልም ነው ያሉት። የሴቶች እና ሕጻናትን ጥቃት ለመከላከል ቅንጅታዊ አሠራር ግድ እንደሚልም አስረድተዋል። የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ብሎም መብታቸውን ለማስከበር ቢሮው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር ስለመዘርጋቱም አቶ ወንድወሰን አብራርተዋል። ፍትሕ ቢሮው ከፖሊስ፣ ከፍርድ ቤቶች እና ከማረሚያ ቤቶች ጋር ተናብቦ እየሠራ ነው ብለዋል።

ፖሊስ ምርመራውን ያካሂዳል፤ ዐቃቢ ሕግ ክስ መስርቶ ይከራከራል፤ ፍርድ ቤት ይወስናል፤ ማረሚያ ቤቶች ደግሞ ሕጉን ተከትለው አጥፊውን ያርማሉ ነው ያሉት። ሴቶች እና ሕጻናት ላይ ጥቃት ከተፈጸመ የጤና፣ የማኅበራዊ፣ የሥነ ልቦና እና ሌሎችም አካላዊ ጉዳቶች ስለሚደርሱ ለዚህ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል።

እንደ ሀገር የሴቶች እና ሕጻናትን ጥቃት ለመከላከል አስተባባሪ አካል ስለመቋቋሙም ጠቅሰዋል። ሥራውን በፌዴራል ደረጃ ፍትሕ ሚኒስቴር ይመራዋል፤ በክልል ደረጃ ደግሞ ለፍትሕ ቢሮ ተሰጥቷል። በዚህ ተዋረድ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

ችግሩ ከተፈጠረ ደግሞ ተጎጅዎችን ለመንከባከብ የተዘጋጀ ማዕከል ስለመኖሩ ገልጸዋል። ወደ ማዕከሉ ለሚመጡ ተጎጅዎች በመጀመሪያ የጤና አገልግሎት ይሰጣል፤ የሥነ ልቦና እና የኢኮኖሚ ድጋፍም ይደረጋል፤ በመቀጠልም የፍትሕ አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት።

ይህ ሁሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ተጎጅዎች በአንድ ማዕከል መሰባሰብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል። የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ተጎጅዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንገላቱ እና ማስረጃዎችም እንዳይጠፋ ያግዛል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ውስጥ በባሕር ዳር፣ ደሴ እና ጎንደር ከተሞች ተጎጅዎች በተማከለ መንገድ የሚስተናገዱባቸው የማገገሚያ ማዕከላት እየተገነቡ እንደኾነ ይታወቃል። የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ በነጻ የሚሰጥ በመኾኑ ተጨማሪ ረጂ ድርጅቶች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በሃሳብ እና በገንዘብ መደገፍ እንዳለባቸውም አቶ ወንድወሰን ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማሠራጨት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የወንዶች አጋርነት ወሳኝ ነው፡፡