
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ 2016/17 የምርት ዘመን በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት የላቀ አፈጻጸም ላበረከቱ አካላት እውቅና የመስጠትና ለቀጣይ የምርት ዘመን የግብዓት አቅርቦትና ስርጭትን በሚመለከት የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና ሌሎችም የክልሉና የፌደራል ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የ2016/17 የምርት ዘመን የጸጥታ እና ሌሎች ችግሮች የነበሩ ቢኾንም በጸጥታ ኃይሉ ርብርብ ከ7 ሚሊየን በላይ ኩንታል ማዳበሪያ በማሰራጨት ውጤታማ ምርት ማግኘት መቻሉን አንስተዋል። በዚህ ጊዜ ተሳትፎ ላደረጉ ኹሉም አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።
ግብርና በየትኛውም ሁኔታ የማይቆም ሥራ በመሆኑ ለቀጣይ የምርት ዘመን የተሻለ ምርት ለማምረት፣ ባለፈው የተሳተፉትን እውቅና በመሥጠት ለማበረታታት እና በቀጣይ ሥርጭቱ ላይ ምክክር ለማድረግ መድረኩ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) መድረኩ የባለፈውን የግብዓት አቅርቦት በመገምገም የቀጣዩን ስርጭት በውጤታማነት ለማሳለጥ ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል።
ምርጥ ዘርንና ማዳበሪያን መጠቀም ምርትን 50 በመቶ መጨመር እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ይህንን መነሻ አድርገው እንደተናገሩት የሀገራችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የግብአት አቅርቦት ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ ነው።
የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ተኩስ የሚከፍቱና የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የሚሠሩ አካላት በመኖራቸው ሰላምን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከባለፈው ዓመት በተሻለ መንገድ ግብዓት ማሰራጨት ያስፈልጋልም ብለዋል።
በባለፈው ዓመት የግብዓት ስርጭት በርካታ አካላት ዋጋ ቢከፍሉም 7 ሚሊዮን ኩንታል ተሰራጭቶ ውጤታማ ምርት መገኘት ችሏልም ብለዋል። ውጤቱ የመጣውም የክልሉ መንግሥት ባደረገው ጥረትና የሀገር መከላከያ ሠራዊት እጀባ እያደረገ ግብዓቱ ወደ አርሶ አደሮች እንዲደርስ በመደረጉ ነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላበረከተው አስቸዋጽኦም ምሥጋና ይገበዋል ብለዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ መንግሥት ለቀጣይ የምርት ዘመን የሚኾን ከ8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ዝግጅት ማድረጉን ለክልሉ አርሶ አደሮች አብስረዋል።ይህም ከባለፈው ዓመት ሲነጻጸር ከ 15 በመቶ በላይ እድገት አለው ብለዋል።
እንደ ባለፈው ዓመት ኹሉ ለቀጣዩ የምርት ዘመንም የተዘጋጀውን የአፈር ማዳበሪያ በተገቢው መንገድ ለአርሶ አደሮች ለማድረስ የባለፈው ዓመት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!