
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፖሊዮ ክስተት መታየቱን ተከትሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመከላከያ ክትባት እየተሠጠ ነው። በአማራ ክልልም ክትባቱ በዘመቻ እየተሰጠ ነው። በሽታውን ለማጥፋት ዓለም አቀፍ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን የጤና ተቋማት ይገልጻሉ። የፖሊዮ በሽታን መንስኤ፣ አስከፊነት፣ መከላከያ እና የማኅበረሰብ ኀላፊነትን በተመለከተ የጤና ባለሙያ አነጋግረናል – እነሆ።
በአማራ ክልል የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የበሽታዎች እና የጤና ኹኔታዎች ቅኝት እና ምላሽ ቡድን አስተባባሪ ጽጌረዳ አምሳሉ ፖሊዮ በቫይረስ አማካይነት የሚመጣ በሽታ መኾኑን ገልጸዋል። በአይነ ምድር በተበከለ ምግብ እና ውኃ እንዲሁም ንጽህናው ባልተጠበቀ እጅ አማካይነት ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ እንደሚችልም አብራርተዋል።
ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭ እና ተጠቂ የኾኑት ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ህጻናት ናቸው።
የእጅ እና የእግር መልፈስፈስ እና ሽባነት የበሽታው ምልክቶች መኾናቸውን የገለጹት ወይዘሮ ጽጌረዳ ሞትም ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅሰዋል። አንድ ጊዜ ምልክት ካሳየ በኋላ የመዳን እድሉን ዝቅተኛነትም አመላክተዋል።
“ፖሊዮን የመከላከያ ብቸኛው መንገድ ህጻናትን ማስከተብ ነው” ያሉት ወይዘሮ ጽጌረዳ ክትባቱ ከተገኘ በኋላ ውጤታማ በመኾኑ ፖሊዮ በመጥፋት ላይ ያለ በሽታ ነውም ብለዋል።
እንደ ቡድን መሪዋ ገለጻ መደበኛ እና የዘመቻ ክትባትን ተከታትሎ በማስከተብ የህጻናትን በፖሊዮ መጠቃትን መከላከል ይቻላል። ነገር ግን አንድ ህጻን በፖሊዮ በሽታ ከተያዘ በኋላ ማዳን አይቻልም። ያለው እድል የመራመጃ ድጋፍ ብቻ ነው።
በዘመቻ የሚሰጠው ክትባት መነሻው በአማራ ክልልም እና በሀገር ደረጃም የፖሊዮ በሽታ መኖሩን አመላካች ክስተት በመታየቱ መኾኑን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ የዘመቻ ክትባቱ ቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በህጻናት ማቆያዎች፣ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ህጻናትን ከፖሊዮ በሽታ ለመታደግ እናቶች፣ ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰቡ እና ክትባቱ የሚሰጥባቸው ተቋማት ክትባቶችን ተከታትሎ ማስከተብ እና መተባበር እንደሚጠበቅባቸው ነው ወይዘሮ ጽጌረዳ ያሳሰቡት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!