
አዲስ አበባ: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሥነ ምግባራዊ ትውልድ ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ መልእክት የአዲስ አበባ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ያዘጋጁት የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው። በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ ኅብረተሰቡ የሙስናን አስከፊነት በመገንዘብ የመከላከል ሥራዎችን ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ ስለመኾኑም ተናግረዋል። በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሙስናን የሚጸየፍና በሥነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ሚዲያው ለሀገር ገፅታ፣ ለትውልድ የሥነ ምግባር ግንባታ እንዲሁም ለብሔራዊ መግባባት በትኩረት እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በፓናል ውይይቱ ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ (ዶ.ር) ወጣቱን ትውልድ በስነ ምግባር በማነፅ በኩል ትምህርት ቤቶች እና ቤተ እምነቶች የችግሩን አሳሳቢነትና ጎጂነት ትምህርት በመስጠትና በማስገንዘብ በኩል ኅላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።
ሙስናን የሚቃወም ትውልድ ለመፍጠር መንግሥት ፖሊሲዎችን በማውጣትና ተፈፃሚነታቸውን በመከታተል፣ ለኅብረተሰቡም በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ በመስጠት በኩል ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መቅደስ ተስፋዬ በሥነ ምግባር የታነፀና ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ በመቅረፅ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ለሀገር ግንባታ ያለው ድርሻ ትልቅ በመሆኑ ያለመድከም መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል። ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ በሕዝቦች መካከል መተማመንና አንድነት እንዲኖር እና ውጤታማ አሥተዳደር ለማስፈን ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ እናትዓለም መለሰ ሚዲያው የመንግሥትን እንቅስቃሴዎች በመከታተልና የዘገባ ሽፋን በመስጠት እንዲሁም ምርመራዊ የጋዜጠኝነት ሥራዎችን በማከናወን የአሠራር ብልሹነትን ለማጋለጥ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን መትጋት አለበት ብለዋል። ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሆነ ሚዲያ ሁሉ በፀረ ሙስና ትግል ውስጥ ትልቅ ኅላፊነት ወስዶ መሥራት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ቤቴል መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!