
ደሴ: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከ23 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁስ ለደሴ፣ ኮምቦልቻ እና አምባሰል ከተሞች ድጋፍ አድርጓል።
የሕክምና ቁሳቁሱ በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት እገዛ ያደርጋል ተብሏል።
የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ሰሜን ምስራቅ ማዕከል መሪ ሞልቤቶ ታደሰ የተደርገው ድጋፍ በዩ ኤስ ኤ አይ ዲ የገንዘብ እገዛ ግዥ መፈጸሙን ገልጸዋል። ተቋማማቱ አለብን ባሉት ክፍተት መሠረት ግዥ መፈፀሙንም ተናግረዋል።
የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ለደሴ፣ ኮምቦልቻ እና አምባሰል ወረዳዎች እንደተደረጉ የተናገሩት መሪው ከ23 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገባቸው አስታውቀዋል። በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሣነወርቅ ለተደርገው ድጋፍ አመስግነዋል። ድጋፉ በሰሜኑ ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ውድመት የደረሰባቸው የሕክምና ተቋማትን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የጤና መምሪያ ኀላፊ ሰይድ የሱፍ ድጋፉ የጤና ተቋሞቻችንን ክፍተት መሠረት ያደረገ በመኾኑ ትልቅ እገዛ ያደርግልናል ነው ያሉት።
የሕክምና ቁሳቁስ ርክክብ ተደርጎ በባለሙያ የተከላ ሥራ እንደሚሠራም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ አበሻ አንለይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!