ነፍጥ ይዞ ጫካ መግባት የሕዝብን ችግር ማባባስ እንጅ ስለማይፈታ መደገም እንደሌለበት ተገለጸ።

6

ወልድያ: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልእክት በሰሜን ወሎ ዞን ደረጃ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

በሰሜን ወሎ ዞን የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ከድር ሙስጠፋ የበዓሉ መከበር ዋነኛ አላማ ልዩነትን በማጥበብ፣ አንድነትን በማጎልበት፣ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባት በመፍጠር፣ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጽያን ለማጽናት ነው ብለዋል፡፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በየዓመቱ የሚከበረው የወል ህልሞቻችንን እውን ለማድረግ፣ የጋራ የብልጽግና ጉዟችን ለማሳለጥ፣ አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ ለመገንባት በጋራ የምንቆሞበትን ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በማለም መሆኑን ገልጸዋል።

የሀሳብ ልዩነቶች መቸም ይኖራሉና አማራጭ ሀሳቦችን ይዞ ፓርቲ መስርቶ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመታገል ይልቅ ነፍጥ አንስቶ ፍላጎትን በኃይል ለማስፈጸም መሞከር ብሔረዊ ጥቅምን እና ሀገራዊ ክብር ይጎዳል ነው ያሉት።

የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን በመቀበል ለመፍታት በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአማራ ሕዝብም በርካታ ጥያቄዎች አሉት፤ ጥያቄዎችን ለመፍታት ቁጭ ብሎ መመካከር እንጅ ነፍጥ አንግቦ ጫካ መውጣት አያስፈልግም ሲሉ አሳስበዋል።

“ጫካ መውጣት የሕዝብን ችግር ያባብሳል እንጅ አይፈታም፤ ሊታረምም ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል። ስለዚህ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይትና በድርድር ብቻ እንዲፈቱ ሁላችንም መታገል ይገባናል ነው ያሉት።

በዓሉ ያለፈውን እና የአሁኑን ብቻ ሳይሆን መጪውን ብሩህ ተስፋ፣ አብሮ የመኖር፣ አብሮ የመበልጸግ፣ አብሮ የመዝለቅ፣ ታላቅ ሀገር የመገንባት ትልማችንን የምናሰምርበት፤ ቃላችንን በአንድነት የምናድስበት፣ በጋራ የምንቆምበት ይሆናል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኤች አይ ቪ ኤዲስ ስርጭትን ለመግታት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተጠቆመ።
Next articleወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከ23 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።