
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የዓለም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን “ሰብዓዊነትን ያከበረ የኤች አይ ቪ ኤድስ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ በደብረ ማርቆስ ከተማ በውይይት ተከብሯል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኅላፊ የሽዋስ አንዱዓለም የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በሽታውን ከመከላከል ባለፈ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት መድኃኒት ያቋረጡ ወገኖች እንዲጀምሩ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊው ተናግረዋል።
በመድረኩ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን በመከላከል በኩል የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተጠቁሟል። ሙዳይ ወጣቶች ጤና ማጠናከሪያ እና ሲ ቪ ኤም ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅትም ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት የቅድመ መከላከል ተግባር እያከናወኑ መኾኑን ኀላፊው ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ኤች አይ ቪ ኤዲስን የመከላከል ሥራ የሁሉም ማኅበረሰብ ድርሻ መኾኑን ገልጸው በሀገር አቀፍ ጀረጃ ሊቀርቡ የሚገባቸው የመመርመሪያ ኪት እና ሌሎች ቁሳቁሶች እጥረት ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝባቸው ከ14 ሺህ 500 በላይ ወገኖች ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ በፀጥታ ችግር ምክንያት ከ400 በላይ የሚኾኑት መድኃኒት አቋርጠው እንደነበር ከጤና መምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!