በአማራ ክልል የሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት ተጀመረ።

15

ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ክልላዊ ሁለተኛው ዙር የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (ፖልዮ) ክትባት ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል። የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ጤና ቢሮ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ከዩኒሴፍ እና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ነው ክትባቱ የተጀመረው።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ ፤ እንደ ሀገር በመጀመሪያው ዙር የተሰጠው ክትባት ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው አሁን ደግሞ ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ መልኩ በቅንጅት ክትባቱ ይሰጣል። በአማራ ክልል በሁለተኛው ዙር መሰጠት በተጀመረው ክትባት ከ4 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን ተደራሽ እንደሚደረግ ነው ዶክተር መልካሙ የተናገሩት።

የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በመጀመሪያው ዙር የተሰጠው ክትባት የእቅዱን 97 በመቶ መሳካቱን አስታውሰዋል። በሁለተኛው ዙር እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት በክልሉ በሁሉም ቦታዎች ክትባቱ ይሰጣል ብለዋል አቶ በላይ። ልጃቸውን ያስከተቡ መምህርት “ክትባቱ ለልጆች አስተዳደግ በጣም አስፈላጊ በመኾኑ ልጄን አስከትቤያለሁ” ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየት ክትባቱ በሽታ ተከላካይ በመኾኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ሊያስከትቡ ይገባቸዋል ብለዋል።

ክትባቱ ከኅዳር 27/2017 እስከ 30/2017 በትምህርት ቤቶች እና ቤት ለቤት በጤና ባለሙያዎች እንደሚሰጥ የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጋራ በመሥራት ሕዝባችንን ከወባ ወረርሽኝ መታደግ ይኖርብናል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleየኤች አይ ቪ ኤዲስ ስርጭትን ለመግታት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተጠቆመ።