
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት በባሕር ዳር ከተማ ለወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማፋሰስ ሥራ ተከናውኗል። በማፋሰስ ሥራው በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ፣ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ እና ሌሎችም መሪዎች ተሳትፈዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በአማራ ክልል በሳምንት ከ80 ሺህ በላይ የወባ በሽታ ተጠቂዎች እየተመዘገቡ መኾኑን ተናግረዋል። ወረርሽኙን ለመቀነስ ብሎም በሽታውን ለማጥፋት በትብብር መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች ለወባ መራቢያ ምቹ የኾኑ ቦታዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ለራሱ ጤና በማሰብ አካባቢውን በትብብር ማጽዳት እና ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን ማፋሰስ እንዳለበትም አሳስበዋል። በተለይም ግንባታ ባለባቸው ቦታዎች ውኃ ያቆሩ ጉድጓዶች እና እቃዎች መኖራቸውን መታዘባቸውን ገልጸዋል።
ግንባታ የሚያከናውኑ ባለሃብቶች ውኃዎችን ተከታትለው በማፋሰስ ሕዝብን ከወባ በሽታ ወረርሽኝ መታደግ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። በጋራ በመሥራት ሕዝባችንን ከወባ ወረርሽኝ መታደግ ይኖርብናል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ በወባ በሽታ አክሞ ከማዳን ይልቅ ቀድሞ መከላከል ላይ መሥራት አለብን ብለዋል።
የማኅበረሰቡ አጎበር የመጠቀም ልምድ መቀነሱንም ገልጸዋል። የጤና ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው አካላት በየማኅበረሰቡ ቀየ እየዘለቁ ስለአጎበር አጠቃቀም እና ፋይዳው ማስተማር እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአማራ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል ለሚያደርገው ጥረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባን ስርጭትን ይገታሉ” በሚል ተነሳሽነት የሚደረገው ክልላዊ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። የትንኝ መራቢያ አካባቢዎችን በማፋሰስ በሽታውን በመቀነስ በኩል ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የበሽታው ስርጭት መጠነኛ መቀነስ ቢታይበትም የመከላከል ዘመቻው እስከ ታኅሳስ 30 ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። ወባን የመከላከል ሥራ ዓመቱን ሙሉ መከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል። የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የወባ በሽታ በባሕር ዳር ከተማ በወረርሽኝ ደረጃ መከሰቱን ገልጸዋል። ይህንን ለመከላከልም ዛሬ ሰባተኛውን ሳምንት የማፋሰስ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። ሥራው በቀጣይ ለ4 ሳምንታት በላቀ የሕዝብ ንቅናቄ ይቀጥላል ብለዋል።
የማፋሰስ እና የማጽዳት ሥራው በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች እንደሚካሄድም ገልጸዋል። “ኅብረተሰቡ ለራሱ ጤና ራሱ መሥራት አለበት” ያሉት ምክትል ከንቲባው ሁሉም የከተማው ነዋሪዎች ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን እንዲያፋስሱ አሳስበዋል። በተለይም በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉ ባለሃብቶች በሥራ አካባቢያቸው የሚገኙ ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስ የሕዝብ ጤና መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!