
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በ2016 የምርት ዘመን የስንዴ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ገልጿል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ እንዳለው አነስተኛ ማሳ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ አርሰው በስንዴ ዘር መሸፈን ችለዋል፡፡
ታርሶ በዘር ከተሸፈነው መሬት ላይ 123 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት እንደቻሉም ነው ያስገነዘበው፡፡ በምርት ዘመኑ በመስኖ ከታረሰው 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 107 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት እንደተቻለም አብራርቷል። የ2016 የምርት ዘመን ላይ የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት 230 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱንም ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የጠቆመው።
ከ2012 የምርት ዘመን ጋር ሲነፃፀርም አነስተኛ ማሳ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች 54 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ብቻ ነበር ያመረቱት። ዛሬ ይህ ቁጥር ትርጉም ባለው መጠን ከፍ ስለማለቱም ነው የገለጸው።
ይህ እመርታ በጽኑ አመራር እና በአስቻይ ፖሊሲዎች ብሎም ምርትን ለማሳደግ በተተገበረ ያላሰለሰ ጥረት የተገኘ እንደኾነም አስገንዝቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!