ሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኀይል እያሠለጠነ እና እያደራጀ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።

80

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ የታየውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ከሕዝቡ የተውጣጡ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኀይሎች እያሠለጠነ እና እያደራጀ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታውቋል። የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በዞኑ የታየውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ የሕዝቡን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት አሥተዳደሩ በትጋት እየሠራ ነው ብለዋል።

ለዚህ መሳካትም በሁሉም ወረዳዎች በሕዝብ ለተመረጡ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪዎች የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ሥልጠና እየተሰጠ ስለመኾኑ ተናግረዋል። ዋና አሥተዳዳሪው ለአሚኮ እንደገለጹት በዞኑ ሰላም እንዲመጣ የመከላከያ ሠራዊት ከክልሉ የፀጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት የከፈለው መሰዋትነት ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ በክልሉ በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ ኀይሎች እና የፖለቲካ መሪዎች ጋር በመቀናጀት በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች የሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ ኀይሎችን በማደራጀት ብሎም በማሠልጠን በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑንም አንስተዋል።

አሥተዳዳሪው የዞኑ ሕዝብ ነፍጥ አንስተው ወደ ጫካ የገቡ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ በመምከር እና ለመከላከያ ሠራዊቱ፣ ከሕዝቡ ለተመረጡ የሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ ኀይሎች ድጋፍ በማድረግ ሂደቱ ላይ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው ከሕዝቡ ተመርጠው ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኀይሎች ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ወደ ሕዝባቸው ሲቀላቀሉ የሚሰጣቸውን ሕዝባዊ ተልዕኮ በመልካም ሥነ ምግባር እንዲወጡም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ምጣኔ”
Next articleኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ አምርታለች።