ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የጤና፣ የሥነ ልቦና እና የፍትሕ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተሠራ ነው።

72

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ ምክንያቶች ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናት በአንድ ማዕከል አርፈው አገልግሎት በማግኘት ከጉዳታቸው የሚያገግሙበት ማዕከል በባሕር ዳር ከተማ ሊገነባ ነው። በግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ፣ የክልሉ ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ተገኝተዋል።

የሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በዓለም ለ33ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የነጭ ሪቫን ቀን በማስመልከት የተለያዩ ንቅናቄዎች እየተደረጉ ስለመኾኑ ተናግረዋል። የሴቶች እና ህጻናትን ጥቃት ለመከላከል ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እየተከናወኑ ነውም ብለዋል።

የሴቶች እና ህጻናትን መብት በተመለከተ የወጡ ሕግ እና ደንቦችን የማስረጽ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በመንከባከብ በኩል ሊደረጉ የሚገቡ የጤና እና የሥነ ልቦና ድጋፎችን ለማጠናከርም የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ግንባታው የተጀመረው ማዕከልም ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ተቀብሎ ለመንከባከብ ሁነኛ ቦታ ነው ብለዋል። ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እንደ በፊቱ ተሸማቅቀው እና ከንፈር እየመጠጡ አይኖሩም፤ ይልቁንም ከጉዳታቸው አገግመው፣ ፍትሕም አግኝተው እና ዘላቂ ድጋፍ ተደርጎላቸው ቀሪ ሕይዎታቸውን ባመረ ሁኔታ እንዲኖሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

ማዕከሉ የምግብ እና የመጠለያ አጠቃላይ አገልግሎት የሚሰጥ ሲኾን ሴቶች የሙያ ሥልጠና የሚያገኙበትም ይኾናል። ቢሮ ኀላፊዋ በባሕር ዳር ከሚገነባው የማገገሚያ ማዕከል በተጨማሪ በደሴ፣ በጎንደር እና በሌሎችም ከተሞች መሰል ግንባታ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት በተደራጀ መልኩ ድጋፍ የሚያገኙበት ማዕከል ከዚህ በፊት እንዳልነበረ ገልጸዋል። በባሕር ዳር ከተማ የሚገነባው ማዕከል በተለያየ ምክንያት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት የሕክምና አገልግሎት እና የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል ነውም ብለዋል።

ጤና ቢሮ ከሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ይህንን ማዕከል እንደሚያሠሩትም ተናግረዋል። በጀቱን ጤና ቢሮው ከተለያዩ ረጅ አካላት እንዳሰባሰበም ተናግረዋል። በ123 ሚሊዮን ብር ወጭ የሚገነባው ማዕከል የግንባታ ሥራው በ270 ቀናት ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ይገባል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሴቶች እና ህጻናትን ከጥቃት መጠበቅ የሁላችንም ኀላፊነት ነው ብለዋል። የማገገሚያ ማዕከሉ እንዲገነባ ከተማ አሥተዳደሩ ቦታ ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ ስለመኾኑ ተናግረዋል። በቀጣይም ይህ ትልቅ ፋይዳ ያለው ተቋም መንገድ፣ ውኃ፣ መብራት እና የመሳሰሉት አቅርቦቶች እንዲሟሉለት በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢንቨስትመንት ዘርፍን ለማነቃቃት እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።
Next article“የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ምጣኔ”