የኢንቨስትመንት ዘርፍን ለማነቃቃት እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።

45

ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጸጥታ ችግር ተጽዕኖ ያሳደረበትን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋል። በአማራ ክልል ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ እንዳስታወቀው የኢንቨስትመንት ሥራዎችን በሰላም እጦቱ ምክንያት በታቀደው ልክ ማከናወን አልተቻለም። ነገር ግን የዞኑን ጸጋዎች ባማከለ መልኩ በአምራች ዘርፍ፣ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበር፣ በብረታ ብረትና እንጨት፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን፣ የጨርቃጨርቅ እና የአገልግሎት ዘርፎችን ለማነቃቃት ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሙሉነሽ ውበቴ በተያዘው በጀት ዓመት ከ300 በላይ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል። ባለፉት አምስት ወራት 20 ለሚሆኑት አልሚዎች ፈቃድ መሠጠቱንም ተናግረዋል። በዞኑ 17 ኢንዱስትሪዎች ግንባታቸው ተጠናቅቆ የማሽን ተከላ ሥራ እያከናወኑ ነው ያሉት ኃላፊዋ ወደ ማምረት ይገባሉ ተብሎ ከታቀዱት 13 ኢንዱስትሪዎች መካከል ሁለቱ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአምራች ዘርፍ ለተሰማሩ ዘጠኝ አልሚዎች ከ3 ሄክታር በላይ መሬት ተላልፏል ነው ያሉት። በግብርና እና አገልግሎት ዘርፎች ለተሰማሩ ሌሎች ስድስት አልሚዎችም የኢንቨስትመንት ቦታ ተላልፏል ብለዋል።

የጸጥታ ችግሩ ተጽዕኖ ያሳደረበትን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊዋ በግንባታ ላይ ባሉና ማምረት በጀመሩ ኢንዱስትሪዎች ከ2 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወገኖች በቋሚና በጊዜያዊነት የሥራ እድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።

የግንባታ መሬት ወስደው ወደሥራ ባልገቡ ዘጠኝ ባለሀብቶች ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዷልም ብለዋል።

በጸጥታ ችግሩ ምክንያት አካባቢውን ለቀው የወጡ ባለሀብቶች እንዲመለሱ እና የተረከቡትን መሬት ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስት ረቂቅ አዋጆችን አጸደቀ።
Next articleጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የጤና፣ የሥነ ልቦና እና የፍትሕ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተሠራ ነው።