ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ አስጀመረ።

56

አዲስ አበባ: ኅዳር 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ባንኩ “25 ዓመታትን በታታሪነት እና በአገልጋይነት” በሚል መሪ መልእክት 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን እያከበረ ነው። የአዲሱ የክፍያ ካርድ የኢዩቤልዩ ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ነው። ባንኩ ያስጀመረው የቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር መኾኑ ተመላክቷል።

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄኖክ ከበደ ባንኩ ከዓለም አቀፍ የክፍያ ቴክኖሎጂ መሪው ማስተር ካርድ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለው ቀድሞ የተከናወነ ስምምነት እንዳለው አስታውሰዋል። ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ መር እንቅስቃሴ በማድረግ የደንበኞችን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የባንኩ ተቀዳሚ ተግባር መኾኑን አንስተዋል።

ምቹ፣ ሁለገብ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የክፍያ መፍትሔን በባንኩ ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል። ደንበኞች ያለምንም እንከን የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ፍላጎታቸውን በቀላሉ የሚያሟላ ለተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ እንዲፈፅሙ የሚያስችል ምቹ አማራጭም መኾኑንም ገልጸዋል።

የገንዘብ ዝውውርን ለማፋጠን የሚያስችል መኾኑን የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው በመላው ኢትዮጵያ በንብ ባንክ ቅርንጫፎች ዝግጁ እንደሚደረግ ገልጸዋል። የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ተወካይ እልፍአገድ አረጋኸኝ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል አገልግሎት በመስጠት እና የደንበኞችን የአኗኗር ዘዴ በመቀየር ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ከንብ ባንክ ጋር አብሮ በመሥራት አካታች ኢኮኖሚን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እንሠራለን ነው ያሉት። ደንበኞች የፋይናንስ አገልግሎትን በዲጂታል በታገዘ መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግብይት እንዲያደርጉ እና ክፍያ እንዲፈፅሙ የሚያስችል መኾኑንም አመላክተዋል።

ዘጋቢ፦ቤቴል መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ቀጣና የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ አባላት ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
Next articleዘሊንክ ምንድን ነው?