
አዲስ አበባ: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ለወደፊቷ የዲጂታል ኢትዮጵያ የብዙኀን ባለድርሻ አካላት ትብብር” በሚል መሪ መልዕክት ብሔራዊ የኢንተርኔት አሥተዳደር ጉባኤ አካሂዷል። በጉባኤው የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በጉባኤው ብሔራዊ የኢንተርኔት አሥተዳደርን ለማሳደግ እና ፈጣን ለማድረግ የሚያስችሉ ሃሳቦች እና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችሉ መሠረታዊ መፍትሄዎች ላይ ውይይት ተደርጓል። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማዕቀፎች የዲጂታል ልማቱን ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የ2025 ዲጂታል ፖሊሲ ዕቅድ የተሳካ እና ዕድገቱ የተፋጠነ እንዲኾን መንግሥት ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመኾን እየሠራ ነው ብለዋል።
ዶክተር በለጠ የሚዘጋጁ የውይይት እና የምክክር መድረኮች ፎረም ፖሊሲዎችን ለማጠናከር፣ የአቅም ግንባታ ውጥኖችን ለማሳካት እና የባለብዙ ባለድርሻ አካላት ትብብርን ለማጎልበት ጠቃሚ ምክሮችን እና ግንዛቤዎችን ለማሳደግ ይረዳሉ ነው ያሉት።
አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ የዲጂታል ዕውቀት ያለውን ወሳኝ ድርሻ በመረዳት መንግሥት የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ፕሮግራም ዕቅድን በመንደፍ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ዶክተር በለጠ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!