
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ ምክንያቶች ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት በአንድ ማዕከል አርፈው አገልግሎት በማግኘት ከጉዳታቸው የሚያገግሙበት ማዕከል በባሕር ዳር ከተማ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ባስተላለፉት መልእክት “የሴቶች እና ሕጻናትን ጥቃት አበክረን እንከላከላለን፤ ጉዳት ከተከሰተ ደግሞ አስቸኳይ መፍትሔ መፈለግ ግዴታችን ነው” ብለዋል።
ዛሬ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የማገገሚያ ማዕከልም ጉዳት የሚደርስባቸውን ሴቶች እና ሕጻናት መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ስለመኾኑ አብራርተዋል። የማገገሚያ ማዕከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። ማዕከሉ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ጤና በመከታተል ለማከም ያገለግላል። የገጠማቸውን የሥነ ልቦና ችግር በማስተካከል፣ በኢኮኖሚም በመደገፍ የተጎጅዎችን ቀጣይ ሕይወት የተቃና ለማድረግ የሚያገለግል ማዕከል መኾኑንም አብራርተዋል።
ማዕከሉ የሚገነባው “ጥቃት ይብቃ” ብለው በሚያስቡ በጎ አድራጊዎች ትብብር ስለመኾኑም ዶክተር ሙሉነሽ ገልጸዋል። ለነዚህ አካላት ምሥጋና አቅርበው ሌሎችም ግለሰቦች እና ተቋማት መሰል ሥራዎችን በማከናወን ሴቶች እና ሕጻናትን ከጥቃት የመከላከል የጋራ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የማዕከሉ ግንባታ በፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ዶክተር ሙሉነሽ ግጭቶች ባሉበት ሁሉ ቀዳሚ ተጎጅዎች ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው ሲሉም ተናግረዋል። አማራ ክልል በተከታታይ በግጭቶች ውስጥ የቆየ ነው፤ በዚህም ሰበብ በርካታ ሴቶች እና ሕጻናት ተጎጅዎች ናቸው፤ ግጭት እና ጦርነትን በማስወገድ ከየትኛውም አይነት ጥቃት ነጻ መኾን እና መልካም ማኅበራዊ መስተጋብርን ማስፈን የጋራ ኀላፊነታችን ነው ሲሉም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!