“የኮሪደር ልማት የዛሬ ብቻ አይደለም የትውልድም ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

54

ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በልማት ሥራዎች ዙሪያ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት አድርጓል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ከተማዋን በጋራ የመገንባት ኀላፊነትም ኾነ ግዴታ አለብን ብለዋል። ከተማዋ ውብ ስትኾን አሻራን ማሳረፍ ይገባል ነው ያሉት። የከተማውን የኮሪደር ልማት ሢሠራ እና ከተሠራ በኋላም ለማኅበረሰቡ መስጠት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የከተማዋ የኮሪደር ልማት የእኔ ነው ብሎ ማሰብ ይገባልም ብለዋል። ለኮሪደር ልማት ሃብት ማዋጣት እንደሚገባም ገልጸዋል። በአቅማቸው ልክ ለከተማዋ ልማት እንደሚያዋጡም ተናግረዋል። ለከተማዋ ልማት የንግዱን ማኅበረሰብ ብቻ ሳይኾን የከተማዋን ነዋሪዎችም ማነቃነቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የሚደነቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል ። የኮሪደር ልማቱን ጥቅም ማስረዳት እንደሚገባም ተናግረዋል። ለከተማዋ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል። እየተሠራ ያለው ሥራ ለልጅ ልጅ የሚኾን መኾኑንም ተናግረዋል። የደኅንነት ካሜራዎች መገጠም ለከተመዋ ደኅንነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የልማት ሥራዎች ተጀምረው እንዳይቋረጡም አሳስበዋል። ለልማት ሥራዎች ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው ነው የተናገሩት። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳር ከተማን በቱሪዝም፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት ይጠበቃልም ነው ያሉት። የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ውበት ከፍ የሚያደርግ መኾኑንም ተናግረዋል።

የከተማዋን ልማት ከፍ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በከተማዋ የደኅንነት ካሜራዎችን እየገጠሙ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የደኅንነት ካሜራዎች የከተማዋ ደኅንነት የተጠበቀ እንዲኾን እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የኮሪደር ልማት የዛሬ ብቻ አይደለም የትውልድ ነው ብለዋል። ከተማዋን ጽዱ እና ለነዋሪዎቿ የተመቸች ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

ከተማችን በጋራ እንሥራት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እናድርጋት ብለዋል። በከተማዋ ደረጃ በደረጃ ለሚገነባው 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ከፍተኛ ወጭ እንደሚያስፈልግ እና የንግዱ ማኅበረሰብም ተባባሪ እንዲኾን ጠይቀዋል። የምንወዳትን ከተማ በአንድነት መሥራት አለብን ነው ያሉት። ከወቃሽ እና ከተወቃሽ አመለካከት በመውጣት ለጋራ ልማት በጋራ መሥራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

ለራሳችን ከተማ ከእኛ በላይ ማንም ሊያስብላት እና ሊሠራት አይችልም ነው ያሉት። ግንኙነታችንን እያጠናከርን በጋራ መሥራት ይገባናልም ብለዋል። የተጀመረው የኮሪደር ልማት ውጤታማ እንዲኾን ድጋፋችሁን እንፈልጋለን ብለዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳታፊ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፋሲል አብያተ መንግሥታት ጥገና አንዱ የገነባውን ሌላው ማፍረስን ሳይኾን ማስቀጠል እንደሚገባ የታየበት ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት አገልግሎት የሚውል ማዕከል በባሕር ዳር ከተማ ሊገነባ ነው።