
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የጎንደር ከተማ ኮሪደር ልማት እና የፋሲለደስ ቤተ መንግሥትን እድሳትን ጎብኝተዋል። ጎንደር የነበራትን ሥልጣኔ የሚያሳይ ቅርስ ኾኖ አሁን ላለው ሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ በመኾኑ ትውልድን ከትውልድ ለማስተሳሰር፣ ቅርሱን ለመጠገን እና ለመንከባከብ በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል።
“የፋሲል አብያተ መንግሥታት ጥገና አንዱ የገነባውን ሌላው ማፍረስን ሳይኾን ማስቀጠል እንደሚገባ የታየበት ነው” ያሉት ዶክተር አብዱ ሁሴን ለቅርስ ጥገናው የታሪኩ አካል መኾናቸው የሚኮሩበት መኾኑንም ተናግረዋል።
የሕዝቡን የረዥም ዓመታት የልማት ጥያቄ ለመመለስ ከዚህ ቀደም ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ታላልላቅ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን አጠናቅቆ ለኗሪዎች ክፍት ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመኾኑም ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ አንስተዋል።
ለክልሉ የኢንዱስትሪ ልማት እንቅፋት ፈጥሮ የነበረውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የኃይል ማከፋፋያ ጣቢያዎችን በመገንባት እና ጥገና በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ መሥራቱን ገልጸዋል።
የክልሉ ሕዝብ ማንነት እና የወሰን ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሠራ መኾኑን አንስተው የጸጥታ ችግር መኖር ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዳያገኙ እንቅፋት እየፈጠረ ነው ብለዋል።
በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ውጤታማ ይኾኑ ዘንድ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት እና የከተማዋ ነዋሪዎች በትኩረት እንዲሠሩ መልዕክት ተላልፏል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!